በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ የቀረበው ትችት፣

የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት እየገነባቸው ያሉትን የከተማ ኮሪደሮች እና ፓርኮች በተመለከተ ከፍተኛ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
ጸሃፊው “Democratizing public spaces” የከተማ ፕላን ወሳኝ አካል መሆኑን ቢቀበልም፣ መንግስት በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ማፍሰሱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዘርፎች እንዳልሆኑ የተለያዩ ነጥቦችን በማንሳት ይከራከራሉ።
👉 የቅድሚያ ጥያቄዎች እና የገጽታ ግንባታ ስጋቶች
ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፣ የመንግስት የብልጽግና ገጽታ ግንባታ ፕሮጀክቶች በህዝቡ ጓዳ ያለውን የኑሮ ውድነትና ጉስቁልና ይሸፍናል ወይ? ሲል ይጠይቃል።
በአገሪቱ ያለው የሰላም እጦት የምዕራባውያን አገራት ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንዲያወጡ እያስገደዳቸው ባለበት ሁኔታ፣ የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ሊያስመዘግብ ይችላል ወይ? እንዲሁም ባለሀብቶች ሊሰሩባቸው በሚችሉ ዘርፎች ላይ መንግስት መሳተፉ ተገቢ ነው ወይ? የሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎችን አንስቷል።
👉 የእርዳታ ጥያቄ እና የገንዘብ አጠቃቀም
የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን በላይ የእርዳታ ፈላጊ ህዝብ እንዳለ መግለጹን ተከትሎ፣ የብልጽግና መንግስት መረጃው የተጋነነ ነው በማለት መካዱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ፣ ጸሓፊው መንግስት በፋሲካ በዓል ወቅት የእርዳታ ድጋፍ ሲያደርግ ያሳያቸው ምስሎች እና ፎቶግራፎች የእርዳታ ፈላጊውን ህዝብ ብዛት እንደሚያረጋግጡ ይገልጻል።
እነዚህ የብልጭልጭ ፕሮጀክቶች ከነዳጅ ባለጸጋ የአረብ አገራት የተኮረጁ መሆናቸውን እና ኢትዮጵያ እንደነዚያ አገራት የተትረፈረፈ ሃብት ስለሌላት ያላትን ሃብት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባት አሳስቧል።
👉 የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እና የፕሮጀክት ትርፋማነት
የኑሮ ውድነቱ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረና የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ዝቅ እያደረገ እንደሆነ ጦና ጠቁሟል። በተጨማሪም፣ ማንኛውም ፕሮጀክት የወጪና ጥቅም ትንተና (Return on Investment – ROI) ሊኖረው እንደሚገባ በመግለጽ፣ የኮሪደር ልማቱ ኢንቨስት የተደረገበትን ገንዘብ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይመልሳል? የጥገና እና የማንቀሳቀሻ ወጪዎችስ ታሳቢ ተደርገዋል ወይ? ሲል ይጠይቃል።
በእነዚህ መመዘኛዎች ብልጽግና የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች “የብልጭልጭና የተለጠጠ የገጽታ ግንባታ ሥራዎች” መሆናቸው አያጠራጥርም ብሏል።
👉 የህዝብ ቅሬታ እና የመንግስት ምላሽ
በአሁኑ ወቅት መንግስት በቢሊየን የሚቆጠር ብር በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ሲያፈስ፣ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት እና ተያያዥ ችግሮች መናፍፋታቸው ከፍተኛ ምሬት ፈጥሯል። የህክምና ባለሙያዎች ጥያቄ፣ የመንግስት ሰራተኞች እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች “የማገኘው ገቢ ለቤት ክራይ፣ ለአስቤዛና ለመሳሰሉት አይበቃኝም” የሚል ቅሬታ እያሰሙ ነው። በመንግስት የተደረጉ የውሃና መብራት ክፍያዎች ጭማሪዎችም በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ምሬት እየፈጠሩ መሆናቸውን ጦና ገልጿል።
በመጨረሻም፣ ጸሓፊው ብልጽግና ከሰላም፣ ከፖሊሲ ሉዓላዊነት እና ከፖሊሲ አቅጣጫ የሚታዩ ችግሮችን ለመጋፈጥ ፍላጎት እያሳየ አለመሆኑን ተችቷል። በእነዚህ የብልጭልጭ ፕሮጀክቶች ላይ እየዋለ ያለው ገንዘብ በትክክል ቢታቀድ የህዝቡን ምሬት ሊቀርፍ እንደሚችል ገልጾ፣ መንግስት በተሳሳተ አቅጣጫው መቀጠሉ አሳዛኝ መሆኑን በመግለጽ “The sunk cost fallacy” በሚለው ሀሳብ ጽሁፉን ደምድሟል።