1000058210

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ በሙስና ተጠርጥረው በታሰሩበት ተተኪዎች ተሾሙ

ይሁን እንጂ ግለሰቦቹ ስለመነሳታቸውም ሆነ ስለመሾማቸው የክልሉ ካቢኔ አባላት ወይም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች አለማወቃቸው ጥያቄ መፍጠሩ ተነግሯል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ ከሶስት ቀናት በፊት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በጂንካ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸው መግለፃችን ይታወሳል

አቶ ታረቀኝ የታሰሩበት ምክንያት ከመስኖ ሥራ ጋር በተያያዘ ሙስና ፈጽመዋል በሚል እንደሆነ ለWT ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

የክልሉ ኦዲት ቢሮ ባካሄደው ምርመራ ተጨባጭ ግኝት ቢያገኝም በጥቅም ትስስር ተጠያቂነትን ባያረጋግጥም፣ የፌዴራል ኦዲተሮች ባደረጉት ተጨማሪ ኦዲት ግኝቶች ተከትሎ መታሰራቸው ታውቋል።

በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የቢሮው ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ታከለ ጌታቸው የተባሉ ግለሰብ በፖሊስ እየተፈለጉ ሲሆን፣ ስልካቸውን አጥፍተው ከአካባቢው መሰወራቸውንም መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ ዜና በሚዲያችን ከወጣ በኋላ ዛሬ ደግሞ በተጠረጠሩት ሰዎች ቦታ ሌሎች ግለሰቦች መሾማቸውና ከሥልጣናቸው መነሳታቸው ተገልጿል።

አቶ አይከል ድንጋይ የዋና ኃላፊነት ቦታን ሲረከቡ፣ አቶ ኢያሱ እንግዳ ደግሞ ምክትል ኃላፊ ሆነው በርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ መሾማቸውን የውስጥ መረጃዎች ለWT ሚዲያ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ግለሰቦቹ ስለመነሳታቸውም ሆነ ስለመሾማቸው የክልሉ ካቢኔ አባላት ወይም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እንደማያውቁ ተነግሯል።

ይህ አካሄድ በርዕሰ መስተዳድሩ ላይ የሕጋዊ አካሄድ ጥያቄን እንደሚያስነሳ የWT ሚዲያ ምንጮች አረጋግጠዋል።