ያዳምጡ
በጋሞ ዞን ዛይሴ ብሄረሰብ ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ እንደሆነ የዛይሴ ብሄረሰብ ተወላጆችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘይሴ ሕዝብ ተወካይ አቶ አብርሃም አሞሼ ተናግረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከዛይሴ ብሔረሰብ ጋሞ ዞን የሚወጡ አዳዲስ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ሰሞኑን በጅምላ በተወሰደው በዚህ በቀል እርምጃ ከ15 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ እንዲሁም ከ18 በላይ ሰዎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከአከባቢው ሸሽቷል፥ የግለሰቦች ቤት መቃጠሉ፣ ንብረት ተዘርፏል፣ በርካታ ሰዎችም በአርባምንጭ ዙሪያ ፖሊስ ጣቢያ እና ሌሎች ወደአልታወቀ ቦታ ተወስደው መታሰራቸው ተነግሯል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን አመራሮች በዛይሴ ብሄረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን የኃይል እርምጃ ውስጥ ሽፋን እየሰጡ እንደሆነም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘይሴ ሕዝብ ተወካይ አቶ አብርሃም አሞሼ ለWT ሚዲያ አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባሉ “ሕገወጥ ታጣቂዎች (ልዩ ኃይል/አድማ በታኝ) እና የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊሶች በዘይሴ ነዋሪዎች ላይ ግድያ እየፈጸሙ፣ ንብረቶቻቸውን እየዘረፉ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ጭምር እየገቡ ሰብዓዊ መብት እየጣሱ፣ በሙሉ በእሳት እያወደሙ ነው።” ብለዋል።
እንደ ህዝብ ተወካዩ አቶ አብርሃም ገለፃ በዛይሴ ህዝብ ላይ ያልተቋረጠ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ ነው፣ አዲሱ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ ከ 25 በላይ ንፁሃን ዜጎች በግፍ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ትዕዛዝ ህይወት እንዲያልፍ ተደርጓል፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች የአካል ጉዳተኛ ሆኗል፣ ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሰው ታስሯል እንዲሁም ከአከባቢው ተሰደዋል ብሏል።
በተጨማሪም አንድ ስሙን መገልፅ ያልፈለገ የአከባቢው ነዋሪ ለWT ሚዲያ እንደገለፀው “አቶ ታገሰ ጫፎ ከዚህ ቀደምም በ2017 ዓ.ም. (በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የዘይሴ ሕዝብ ተወካይ የነበሩት አቶ አብርሃም አሞሼ የሕዝቡን ጭቆና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲያቀርቡ፣ ድምጹን ለማፈን ሞክረዋል በሚል ከሷል።
አክለውም “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ብልሹ አሠራሮችን ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ በቸልተኝነት በመመልከት፣ ይህ ድብቅ ሥራ እንዳይጋለጥ እና ፌዴራል መንግሥት በሕግ እንዳይጠይቃቸው አቶ ታገሰ ጫፎ ከላይ ሆነው እየሰሩበት ያለው ሥራ አሁን ላይ ይፋ መውጣት ጀምሯል” በሚል ገልጿል።
አስተያየት ሰጪው “ከጥቂት ወራት በፊት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልሹ አሠራሮች ዙሪያ ለሦስት ቀናት በዎላይታ ሶዶ ውይይት ተካሂዶ የነበረው ውይይት በማስታወስ በወቅቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በበርካታ የብልሹ አሠራር ነጥቦች ተይዘው እንደነበርና በወቅቱ ከሥራቸው ይታገዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ አቶ ታገሰ ጫፎ ሽፋን በመስጠት ዳግም ዕድል እንዲያገኙ ማድረጋቸው በአከባቢው እስካዛሬ ድረስ ችግሩ እንዲቀጥል ማድረጉን ጠቁመዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ጥሪና ያልተሰጠ ምላሽ
የአካባቢው ነዋሪዎች የሚመለከታቸው አካላት በእነዚህ ክስተቶች ላይ በአስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉና እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በተጨማሪም፣ የዛይሴ ብሔረሰብ የራሱን የአስተዳደር መዋቅር ለማግኘት ባቀረበው ሕጋዊ ጥያቄ ሽፋን የጋሞ አመራሮች እየፈጸሙት ነው ያሉትን በደል እንዲቆም ተማፅነዋል።
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለWT ሚዲያ እንደገለፀው፣ የችግሩ መነሻ በአካባቢው የቆየው የዛይሴ ብሔረሰብ የመዋቅር ጥያቄ ጋር የተያያዘ ጠቅሰው መንግሥት በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ሊያስቆምና ተጠያቂነት ሊያስፋፋ እንደሚገባ በመግለጽ፣ ሰላማዊ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥሪ አቅርቧል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለWT ሚዲያ በሰጡት ቃል፣ “ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስከፊ በሆነ የርሃብና ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኝ ገልፀው ይህ ሁኔታ የተፈጠረው በፀጥታ ኃይሎች እየተወሰደ ባለው የኃይል እርምጃ ምክንያት ነው። አሁንም ሰው ማሳ ውስጥ እንዳይገባ ተከልክሎ የገቡትም እየተገደሉ ናቸው፣ ብዙዎቹ የተገደሉትን ቤተሰብ ለማንሳትና ገብቶ ለመፈለግም ተከልክሎ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።” ብሏል።
በተለይም አሁን የጤፍ መሰብሰቢያ ጊዜ በመሆኑ፣ ማሳ መግባት መከልከሉ ባለቤቶቹ ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያጡ እያደረጋቸው ነው። ከዚህ የከፋው ደግሞ ማሽላ የሚጠብቁትንም ሰዎች ከማማ ላይ እየገደሉ በመሆኑ፣ ማሽላውም በወፍ እየተበላ እንደሆነ ገልጸዋል።


ይህ ሁኔታ ሕዝቡ የዕለት ጉርስ ምንጩን እንዳያገኝ በማድረግ ለከፋ ርሃብ እየዳረገው ነው። ነዋሪው አክለውም፣ “ሰው አሁን ግማሹ ተሰደው ወደ አጎራባች ቀበሌዎች የቀሩት ማንም ወደ ማሳ እንዳይገባ ተብለው እንደ አርሶአደር አኗኗር ሰው የየዕለቱን አስቤዛ ከማሳ ነበር የሚያመጣው አሁን ግን ቁጭ ብሎ በርሃብ እየተሰቃዩ ነው ያሉት።”
“እየተወሰደ ያለው የበቀል እርምጃ በግልጽ የዘር ማጥፋት ወንጀል ድርጊት ስለሆነ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በማንነታቸው ምክንያት እየደረሰ ያለውን የንፁሐን ዜጎች ግድያ፣ እስር፣ ስደትና ቤትና ንብረት በእሳት ማውደም አሳዛኝ ድርጊት እንዲያስቆምል በፈጣሪ ስም እንማፀናለን” ብሏል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በመጨረሻም፣ ፌዴራል መንግሥት በአስቸኳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጣልቃ በመግባት ለብሔረሰቦቹ መብት ማስከበር እንዳለበት እና በግለሰቦቹ ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጥሪ አቅርቧል።
ያዳምጡ