በዎላይታ ከ800 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሶዶ ደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ህንጻ ተመረቀ

በምረቃው ላይ መልዕክት ያስተላለፉ አካላት፣ ይህ ህንጻ ለክልሉ አልፎ ተርፎም ለአገር ትልቅ የቱሪዝም መስህብ እና የሚዳሰስ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ ትልቅ ቁሳዊ ሀብት ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለበትም አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌሎች ቤተ እምነቶች ሁሉ፣ የምዕመናንን መንፈሳዊ ህይወት በማነጽ፣ ለግዛትና ለህዝብ አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ተገልጿል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በዜማ፣ በትምህርት፣ በኪነ ህንጻና በኪነ ጥበብ ያበረከተችው አስተዋጽኦ፣ ከመንፈሳዊ ፋይዳው ባሻገር ብዙ ቱሪስቶች አገራችንን እንዲጎበኙ በር ከፍቷል ተብሏል፡፡
በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የእርዳታ እጇን በመዘርጋት፣ የተጎዱ ወገኖችን በአካል በመጽናናትና አምላካዊ ቃልን በማካፈል ቀዳሚ እንደሆነች ተነግሯል፡

፡ የዞኑ አስተዳደርም በቤተክርስቲያኒቱ በተለያዩ አካባቢዎች ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት አስተዳደራዊ ምላሽ መስጠቱን ጠቅሷል፡፡
እንደሌሎች ቤተ እምነቶች ሁሉ ለቤተክርስቲያኒቱ የሚደረጉ አስፈላጊ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተመልክቷል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ቦታ ካላቸው ጥቂት ቅዱሳን መካከል አንዱ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ጻድቁ አባት ከኢትዮጵያ ውጪ በግብጽና በሮም የሚከበሩ እንዲሁም በግብጽና በኬንያ በስማቸው ገዳም ያላቸው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ናቸው ተብሏል፡፡
የዎላይታ ታሪክ ሲነሳ የክርስትና ታሪክ ቀድሞ እንደሚነሳና የወላይታ ክርስትና ሲነሳ ደግሞ ጻድቁ ተክሌ ኃይማኖትና ታላቅ ተጋድሏቸው አብሮ እንደሚነሳ ተጠቅሷል፡፡ የዎላይታ ሶዶ ደብረ መንክራት አቡነ ተክሌኃይማኖት አንድነት ገዳምን የመሰረቱትም እርሳቸው መሆናቸው ታውቋል፡፡

ይህ ቦታ የወላይታ ክርስትና መነሻ፣ የወላይታ ህዝብ የክርስትና እና የስልጣኔ ምንጭ እንዲሁም የህግና የስርዓት መፍለቂያ ቦታ ነው ተብሏል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትን ወደ ኢትዮጵያ መላክ ባቆመችበት ጊዜ፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው የተሾሙ አባት መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
ገዳሙ ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ ቅርሶች የሚገኙበት፣ የቅዱሳን አባቶችና የሊቃውንት መፍለቂያ፣ ታላላቅ መንፈሳውያን አባቶች ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ ያስተዳደሩበትና ያስተማሩበት፣ በኋላም የኢትዮጵያ 3ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት (አባ መላኩ) ለ42 ዓመታት ወንጌል ያስተማሩበት መሆኑን ተጠቅሷል፡፡
የዎላይታ ህዝብ መንፈሳዊም ሆነ ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኝ 24 ትምህርት ቤቶችን ማቋቋሙም ተገልጿል፡፡
በዎላይታ ሶዶ ከተማ በተክለሃይማኖት ገዳም ዙሪያ 11 ክፍሎች ለአቅመ ደካሞች በማሰራት፣ ራሳቸውን ለመርዳት ለማይችሉት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ በማቅረብ ሐዋርያዊ ግዳጃቸውን መወጣታቸውም ተነግሯል፡፡
ይህ ገዳም ከኢትዮጵያ ነገስታት አጼ ሚኒልክ አንድ ጊዜ እና አጼ ኃይለ ስላሴ ሶስት ጊዜ የጎበኙትና ስጦታ ያበረከቱለት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ማጠናከሪያና ለመተዳደሪያ መሬት የፈቀዱለት ታሪካዊ ቦታ ነው ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ በሚከተለው የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ፣ የቱሪዝም ኢኮኖሚን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ታሪካዊውና ጥንታዊው ገዳም ባለቤት በመሆኑ፣ ለቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን መደረግ እንዳለበትም አመላክቷል፡፡
“ስንያያዝና ስንደጋገፍ የማንወጣው ተራራ የለምና፤ እንደዚሁም ደግሞ ለዞናችን ሰላምና ልማት እጅ ለእጅ በመያያዝ ዳግም ታሪክ እንድትሰሩ የተከበረ ጥሪዬን አቀርባለሁ” የሚል መልዕክትም ተላልፏል፡፡