“በንግድ ስራ” እንዲሁም “ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን” መከተል አለባት ብላለች

አሜሪካ ኢትዮጵያ የባህር በር ተደራሽነቷን “በንግድ ስራ” እንዲሁም “ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ በሆኑ አማራጮች” ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለጹ።
ጉዳዩ የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ግምት ውስጥ በማስገባት ወሳኝ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ባለበት ሁኔታ እና ዕድገቱም እንደሚቀጥል የሚያመላክቱ ትንበያዎች መኖራቸውን ገልጸው “የባህር በር ተደራሽነትን ማስፋት ጠቃሚ ነው” ሲሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።
“እንደዚህ አይነት ጥረቶችን መደገፍ የአሜሪካ መንግስት እና የእኔ ኤምባሲ ወደፊትም የሚሰሩበት ጉዳይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም ዋሽንግተን ይህን ጉዳይ እንደምትገነዘበው ተናግረዋል።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ስላላት ግንኙነት ሲናገሩም፣ የአሜሪካ አቀራረብ ኢትዮጵያ በቀጠናው ስፋት ያላት ሀገር ከመሆኗ ጋር እንደሚገናኝ ተናግረው ነገር ግን “ከስፋቷ የበለጠ አስፈላጊው ደግሞ በቀጠናው ያላት ተፅዕኖ እና ቀጠናውን እንደገና ለማረጋጋት ያላት አቅም” ነው ሲሉም አክለዋል።
ይህ የዩናይትድ ስቴትስ መሰረታዊ አቀራረብ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና “ዩናይትድ ስቴትስ የምታደርገው ነገር ማዕከላዊ ነጥብ ይሆናል” ሲሉም አረጋግጠዋል።