በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከፖለቲካ በተጨማሪ የርዕሰ መስተዳድሩ የኢንቨስትመንት ቁማርና ባለሀብቶችን ማሳደድ እስከመቼ ይቀጥላል ?
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በተለይም በዎላይታ ሶዶ ከተማ እና አካባቢዋ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መስተጓጎላቸው እና አስተዳደራዊ ችግሮች መኖራቸው የዜጎችን ስራ የማግኘት እድል እየገደበ መሆኑን የWT ሚዲያ በተደጋጋሚ ዘግቧል።
የኢንቨስትመንት ቁማር እና የባለሀብቶች ስደት ለምን ?
በዎላይታ ሶዶ ከተማ እና አከባቢው ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት ጥያቄዎች ሆን ተብሎ እንዲዘገዩ አልፎ ተርፎም ውድቅ እንዲሆኑ መደረጉ፣ ባለሀብቶች ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌሎች ዞኖች እንዲኮበልሉ እያደረገ ነው።
በተለይም በሪዞርትና ሆቴል ዘርፍ ለመሰማራት ያቀረቡ ፕሮጀክቶች መሬት ባለማግኘታቸው ወደ ሌላ ቦታ እየሄዱ ሲሆን፣ ለዓመታት ሳይወሰን የቀሩ የመሬት ውሳኔዎችም አሉ።
ይህ ሁኔታ የአካባቢውን ሁለንተናዊ እድገት የሚያደናቅፍ እና የንግዱን ማህበረሰብ የሚያሳድድ ግልጽ የከተማዋን እድገት ወደኋላ የመመለስ እቅድ አካል እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር፣ በህጋዊ መንገድ መሬት ተረክበው ፋብሪካዎችን በመገንባት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የጀመሩ ባለሀብቶች እንቅስቃሴ እንዲቆም እና እንዲስተጓጎል እየተደረገ መሆኑን ለWT ሚዲያ የደረሱ መረጃዎች ያሳያሉ።
አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የግል ባለሀብት ለWT ሚዲያ እንደገለጹት፣ ክልሉ ባለሀብቶችን ከመደገፍ ይልቅ ያልተገባ ጫና እየፈጠረባቸው ሲሆን፣ የሚመለከተው የፌዴራል አካል ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የመሬት አጠቃቀምና የህግ ተጠያቂነት የለም ወይ ?
በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ጠበቃ ለWT ሚዲያ እንደገለጹት፣ ባለሀብቶች ለረጅም ጊዜ መሬት ተረክበው ሳያለሙ ወይም ላልተፈለገ ዓላማ ካዋሉ፣ ህጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ለቀጣይ ኢንቨስተሮች ትምህርት እንደሚሆን አብራርተዋል።
ምሁሩ አክለውም፣ ከዚህ በተቃራኒው የክልሉ መንግስት የአንድን አካባቢ ባለሀብቶችን ከሌላው ዞን በተለየ መንገድ ከማጉላላት እና ጫና ከመፍጠር ይልቅ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ወደ ልማት እንዲያስገባቸው አሳስበዋል።

የፍትሃዊነትና ዕኩልነት እጦት ወደየት ያመራ ይሁን ?
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአስተዳደር እና የፖለቲካ ማዕከል በዎላይታ ሶዶ ከተማ ሆኖ ቢቋቋምም፣ የክልሉ ህገመንግስት የዚህን እውነታ በግልጽ አለመቀበሉ እና ዋና ዋና የቢሮ መዋቅሮች በኪራይ ቤቶች መቀመጣቸው ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ አብዛኛው የቢሮ ኪራይ ለመንግስት ተቋማት የሚከፈል ቢሆንም፣ ከሌሎች 5 የክልሉ ማዕከላት ልዩ አድረጉ በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ በአርባምንጭ ከተማ ግን ግለሰቦች ስልጣንን ተጠቅመው በቢሮ ክራይ ሰበብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የመንግስት ሀብት ለግል ጥቅም እያዋሉ መሆናቸው ተዘግቧል።
ይሄንን እውነታ የWT ሚዲያ ባደረገው ዳሰሳ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ እና የሀብት ክፍፍል ኢፍትሃዊነት እንዳለበት ምሁራን ይጠቁማሉ።
ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ የገቢ ምንጭ፣ የተማረ የህብረተሰብ ክፍል እና የንግድ እንቅስቃሴ ባለበት ዎላይታ ዞን ላይ የሚደረገው አድሎአዊ አሰራር በክልሉ መልካም አስተዳደር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ሙስናና የአድሎአዊ ልማት ስጋት እስከመቼ ?
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሙስና፣ በስልጣን አላግባብ መጠቀም እና በግል ጥቅማጥቅም የተሳሰሩ ግንኙነቶች እየበዙ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።
በተለይም በዎላይታ ዞን እና በጌዴኦ የሚገኙ ትላልቅ ድርጅቶች ግብር ከፋይ ባለሀብቶች ላይ ያለአግባብ ጫና በመፍጠር ፋብሪካዎች እንዲዘጉ፣ ባለሀብቶች እንዲታሰሩ እና እንዲሸማቀቁ እየተደረጉ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉን አሰራሮች በመጣስ የትውልድ አካባቢያቸው በሆነችው ጋሞ አርባምንጭ ከተማ ላይ ብቻ ለማተኮር መቁረጣቸው ቅሬታዎችን እያስነሳ ነው።
ሶዶ ከተማ የክልሉ አስተዳደር መቀመጫ ብትሆንም፣ አቶ ጥላሁን ከበደ ዋና ዋና የክልል ስብሰባዎችን እና ኢንቨስትመንት መሳብ የሚችሉ መድረኮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እያዘዋወሩ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በኮንሶ፣ በጌዲኦ፣ በጎፋ እና በሌሎች ብሔሮች ላይ ልማት እንዳይሰራ በማድረግ የራሳቸውን አንድ ብሔር ላይ ብቻ ልማት እየሰሩ ነው ተብሏል።
ለክልሉ የሚመጣ ኢንቨስትመንት በሙሉ ወደ አርባምንጭ ብቻ በግድ እንዲሄድ ሲደረግ፣ ወደዚያ መሄድ ካልፈለጉ ለባለሀብቱ ኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደማይሰጥም ታውቋል።
ክልሉ 32 ብሄር ብሄረሰቦችን ያቀፈ ቢሆንም፣ የልማት ትኩረቱ በአንድ አካባቢ ላይ ማተኮሩ በሌሎች የክልሉ ከተሞች እና ብሔረሰቦች ዘንድ የመገለል ስሜት እየፈጠረ ሲሆን ይህ ኢፍትሃዊነት እና አድሎአዊ አሰራር በጊዜ ካልተስተካከለ ሌሎች መዘዞችን ሊያስከትል ስለሚችል የሚመለከተው አካል ፈትሾ መፍትሄ እንዲሰጥ በርካቶች ይጠይቃሉ።