በኢዲስአበባ ከ260 በላይ የዎላይታ ድቻ ደጋፊዎች ታስረው እንደሚገኙ ተገለፀ።
በተጨማሪም፣ ቤተሰቦቻቸው የት እንደታሰሩ የማያውቋቸው በርካቶች መኖሩ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ከ260 በላይ የዎላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ታስረው እንደሚገኙ ተገልጿል።
ይህ መረጃ የክለቡ አመራሮች ደጋፊዎች አልታሰሩም ማለታቸውን ተከትሎ የወጣ ሲሆን፣ የደጋፊዎች ቁጣን ቀስቅሷል።
በቺርቆስ፣ ፖፖላር፣ የካ፣ ላጋር፣ ኮልፌ፣ ቄራ፣ ላንቻ እና ጎተራ ፖሊስ ጣቢያዎች በርካታ የዎላይታ ድቻ ደጋፊዎች በእስር ላይ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ በእነዚህ ደጋፊዎች ላይ ክስ እንደተመሰረተባቸውም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የክለቡ አመራሮች ደጋፊዎች አልታሰሩም ሲሉ መናገራቸው ሁኔታውን ይበልጥ አወሳስቦታል።
ደጋፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ የክለቡ አመራሮች የደጋፊዎችን ጉዳይ በዚህ ልክ ይክዳሉ ብሎ ማንም እንዳልጠበቀ ገልጸዋል።
“የደጋፊው እና የክለቡ አመራር አይመጣጠኑም” ያሉት ደጋፊዎች፣ አመራሮቹ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበዋል።
ባለፈው ዕለት የሞተ ሰው ባይኖርም፣ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው እና ህክምና እየተደረገላቸው ያሉ ደጋፊዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ደጋፊዎች የታሰሩት ወዲያውኑ እንዲፈቱ እና የክለቡ አመራሮች ለፌዴሬሽኑ ግልጽ ደብዳቤ እንዲያስገቡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።