የሁለተኛ ደረጃ ከተማን መንፈግ የዎላይታን ብሔረተኝነት ያዳክማል ወይስ ያባብሳል? ኢትዮጵያን የብሔረሰቦች እስር ቤት ያስባላት ምን ነበር?
(በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የWT ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ)

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብልጽግና አመራሮች በሚሰጠዉ ስልጠና ላይና በተለያዩ መድረኮች ላይ የዎላይታ ሶዶ ከተማ የሚገባትን ደረጃ እንዳታገኝ በፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብነት የተወሰነዉን ዉሳኔ በተዘዋዋሪ መንገድ የሌላ ከተማን ስም እየጠሩ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ይህ ሕገመንግሥታዊዉን የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መርህ በሕዝብ ብዛት ብቻ እንኳን ብናይ፣ የሚጥስና ሸፍጥ መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር የሆነ ተግባር ነው። ብሔረተኝነት ሳይንሳዊ ትርጉሙ ቤት(ሐገር) ያፈራዉን በእኩልነትና ፍትሐዊነት ልቋደስ ማለት።
ብሔረተኝነትን አዳክማለሁ፣ ብሔሩን እሰለቅጣለሁ እና የመሳሰሉ የፖለተካ ግቦችን በማንገብ፣ ብሔርን ነጥሎ መጨቆን፣ ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል አለመኖር፣ አሳታፊ የፖለቲካ ከባቢ አለመኖር፣ የቀንቋና የባሕል መብትን አለማክበር፣ በጥቅሉ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን አለማክበር ብሔረተኝነትን ቢያባብስ እንጂ የሚያዳክም ሊሆን አይችልም በዘመናዊው አለም።
በዚህ ሕዝብ በነቃበትና የሰለጠነዉን አለም አካሄድ በሚያዉቅበት ዘመን የብሔር ጭቆናን መፈጸም አላዋቂነትን ብቻ ነው የሚያሳየዉ። የዎላይታ ብሔረተኝነት እንቅስቃሴ ሁሌ የሚጠቅሰዉ መነሻ፣ ሐገር ነበርን የሚልና በመንግሥትነት በኖረባቸዉ ዘመናት የነበሩትን የነገስታት ብዛት ይጠቅሳል።
አካባቢዉ የበለጸገ እንደነበረ፣ በፈጠራ እንደሚታወቅ ለምሳሌ ልብስን ከጥጥ ቀድሞ እንደሸመነ፣ ሳንቲም እንደፈጠረ፣ ስልክ በአፍሪካ ቀድሞ እንዳስገባ፣ ባሊሞላ የሚባል ፓርላማ እንደነበረዉ፣ አምራችና የላቀ የንግድ ተሳትፎ እንደነበረዉ፣ ዳልቦ የምትባል በወቅቱ በአፍሪካ የተሻለች የተባላት ከተማ እንደነበረችዉ፣ በወቅቱ ጥሩ የሚባል የአስተዳደር ሥርዓት እንደነበረዉና የመሳሰሉትን ይጠቅሳል።
ይሄን ሲል በግልባጩ በኢትዮጵያ ዉስጥ ከገባሁ በሁዋላ ወደሁዋላ እንድቀር ሆን ተብሎ ተሰርቷል፣ ብዙ መከራና ግፍ ደርሶብኛል፣ ከፖለቲካና ኢኮኖሚያዊዉ ተገልያለሁ ባሕልና ቋንቋዬ ቦታ አልተሰጠዉም የራስን እድል በራሴ የመወሰን መብቴ እንደተነፈገ ቀጥሏል፣ የሐገረ መንግስትም ሆነ የብሔረመንግስቱ ግምባታ ሙሉ ባላገር ወይንም ዜጋ ሊያደርገኝ አልቻለምና የመሳሰሉ ክሶችን ያነሳል።
ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በአጼ ሚኒሊክ ስትፈጠር ወዶ ገብ ወይንም በፈቃዳቸዉ የገበሩ አካባቢዎች አሉ፤ ከዛ ዉጪ መጠናቸዉ የተለያዩ ግጭቶችን አድርገዉ ተሸንፈዉ በኃይል የገበሩም አሉ። ከዚህ ሁሉ ግን እጅግ ከባድ በሚባል ደም አፋሳሽጦርነት ኢትዮጵያ የተቀላቀለዉ ዎላይታ ነው። ከዛም በኃላም በጋሻ የገበረ በሚል ከባድ የሰቆቃ ዘመናትን አሳልፏል።
የሰለጠነዉ አለም በጋሻ የገበሩ ለሚላቸዉ ሕዝቦቹ ቅሬታቸዉን በመቅረፍ ሐገሩን እንዲቀበሉ ቅድሚያ ይሰጣቿል፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁንም በድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ የሚመሩ ፖለቲከኞች ስላሉ ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም።
ከከተማ ጋር ተያይዞ በቀላሉ በአንድ ክልል የሚኖሩ ሕዝቦች ግልጽ መሥፈርት ወጥቶ በዛዉ ልክ መልማት እንዳለባቸዉ ይታወቃል፣ በዚህም በቀላሉ ዎላይታ ሶዶ የክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ብሔር ከተማ እንደመሆኗ የመጀመሪያዉ ሥፍራ ሊሰጣት እንደሚገባ ማስረዳት የአንባቢን እዉቀት መናቅ ነውና እተወዋለሁ።
ከዛ ባለፈ ግን ዎላይታ እንደማንኛውም ወዶ ገብ ብሔር በጅምላ ሊታይ አይችልም።
“በቀድሞ ታሪኬ በአፍሪካ ቀንድ ገናና ነበርኩ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ በመግባቴ ታፍኛለሁ፣ የራሴ መንግስት በነበረኝ ጊዜ በአፍሪካ ደረጃ የሚጠቀስ ቴክኖሎጂ ቀድሞ የሚገባባት ከተማ ነበረችኝ፣ አሁን በኢትዮጵያ ዉስጥ በግልጽ የሚገባኝን የሁለተኛ ደረጃ ከተማ ባለቤትነት እንኳን በሸፍጥ ተነፍጌያለሁ፣ ድሮ በቀዬዬ ያሻኝን ልማት አለከልካይ እሰራ ነበረ፣ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ከሆንኩ ወዲህ ታሰርኩ” እንደሚል ይታወቃል።
በመሆኑም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የናዱ አካሄዶች ብሔረተኝነትን ያቀጣጥላሉ እንጂ አያዳክሙም።