1000060957

የዎላይታ ድቻ ቦርድ በዋንጫው ውዝግብ እና በቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ ዝግጅት ላይ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የዎላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ ቦርድ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን በተመለከተ እና አሁን ያለውን የፕሪሚየር ሊግ ደረጃ በመገምገም የተለያዩ ወሳኝ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታወቀ።

ክለቡ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የተሻለ ዝግጅት መደረጉን ገልጿል።

በዚህም መሰረት፡- ከዳኞች አመዳደብ ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለሚመለከታቸው አካላት አስቀድሞ የማሳወቅ ስራ ተከናውኗል።

በሀዋሳ አርቲፊሻል ስታዲየም ሊደረግ የነበረው ጨዋታ በባለሜዳው በኩል ጫና ሊኖር ይችላል በሚል ስጋት ህጋዊ ጥያቄ በማቅረብ ጨዋታው ገለልተኛ በሆነ ስታዲየም አዲስ አበባ እንዲደረግ ተደርጓል።

ለደጋፊዎች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ተከታታይ ስልጠና በመስጠት እና በትራንስፖርት በማመቻቸት ለጨዋታው መሄዳቸው ተረጋግጧል።

ከዞን መንግስት ጋር በመተባበር የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለተጫዋቾች የስነ-ልቦና ዝግጅት እና የማበረታቻ ስራዎች ተከናውነዋል።

ቦርዱ በጨዋታ ወቅት እና ከጨዋታ በኋላ የተከሰቱ ተግባራትን አስመልክቶ በደረሱ በደሎች ዙሪያ ቀጣይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ደጋፊዎች በአዲስ አበባ በሰላማዊ መንገድ ክለቡን ለመደገፍ ከደረሱ በኋላ ጨዋታው በዝግ ስታዲየም እንዲካሄድ መወሰኑ የደጋፊዎችን እና የህዝቡን ስነ-ልቦና በእጅጉ እንደጎዳ ቦርዱ ገልጿል።

በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ ደጋፊዎችን አስመልክቶ ቦርዱ ከዞን መንግስት ጋር በመነጋገር አብዛኞቹን የማስፈታት ስራ መስራቱን እና የቀሩትንም ለማስፈታት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል።

ምንም እንኳን የዳኝነት ስጋት አስቀድሞ መጠቆሙ ቢገለጽም፣ ክለቡ ግልጽ እና አግባብነት የሌለው የዳኝነት በደል እንደደረሰበት እና በዚህም ምክንያት ዋንጫውን ያለአግባብ እንደተነጠቀ ቦርዱ አሳውቋል።

ቦርዱ በወቅቱ የደረሰውን በደል አስመልክቶ የስፖርት ህጉ በሚፈቅደው መንገድ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ማቅረቡን ገልጿል።

የቀረቡት አቤቱታዎች አጽኖኦት ተሰጥቷቸው ለሌሎች ክለቦችም አስተማሪ በሆነ መንገድ እና የስፖርት ህጉን በተከተለ መንገድ ተግባራዊነቱ እንዲረጋገጥ እና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ቦርዱ ጠይቋል።

በተጨማሪም ቦርዱ ያለአግባብ የተወሰደውን ዋንጫ ለክለቡ እንዲመለስ በህግ አግባብ ለሚመለከታቸው ሁሉ ማመልከቻ መድረሱን አስታውቋል።

ክለቡ ተገቢው ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በህጉ መሰረት ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አስታውቋል።

ቦርዱ ክለቡ አሁን ያለበትን አቋም፣ የነበሩ ክፍተቶችን፣ የውስጥ ችግሮችን እና የቡድን ጉድለቶችን በተመለከተ ዝርዝር ግምገማ በማድረግ እርምት እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

የጉዳዩን ሂደት በቅርበት የሚከታተል ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩንም ክለቡ ገልፀው ይህ ኮሚቴ በነገው ዕለት ማክሰኞ ማመልከቻውን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደሚንቀሳቀስ ታውቋል።