“የቁጫ ማንነት አውልቃችሁ ጋሞ ካልሆናችሁ በቁጫ መኖር አትችሉም” በሚል የሚካሄድ ድብደባና እስራት ፓርቲው በጽኑ አውግዟል።
የቁጫ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሰላምና መግባባት ጉዳዮች ኃላፊ በሆኑት ወ/ሪት ሙሉነሽ ኃይሌ ጫንቃሎ ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈጸመውን እስር በጽኑ አውግዟል።
ቁሕዴፓ ለWT ሚዲያ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ወ/ሪት ሙሉነሽ ኃይሌ ጫንቃሎ የሰላምበር ከተማ ነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ለማግኘት ወደ ጎርማ ቀበሌ ጽ/ቤት ባቀኑበት ወቅት፣ “የቁሕዴፓ አመራር እና አባል በቁጫ መኖር አይችልም” በሚል የመታወቂያ አገልግሎት እንደተከለከሉ እና አካላዊ ጥቃት በመፈጸም የሚያስፈራሩ ዛቻዎች እንደደረሱባቸው ተመልክቷል።

ፓርቲው ይህንኑ ሕገ-ወጥ እስር “የሽንፈትና የክሽፈት ፖለቲካ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ የሃሳብ ታጋዮችን በማሰር የፖለቲካ እምነታቸውን ለማጥፋት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት የሰላማዊ ታጋዮችን የሃሳብ የበላይነት ማሸነፍ እንደማይችል አጽንኦት ሰጥቷል።
ቁሕዴፓ በመግለጫው፣ ወ/ሪት ሙሉነሽ ኃይሌ ጫንቃሎም ሆኑ ሌሎች በተለያዩ የቁጫ አካባቢዎች በፓርቲያቸው አባልነትና በቁጫ ብሔር ማንነታቸው ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።
በተጨማሪም፣ እነዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲቆሙ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ለፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና ለመላው የቁጫ ሕዝብ ገልጿል።
መግለጫው በሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. የወጣ ሲሆን፣ ፓርቲው “ዴሞክራሲያዊነት ከትግላችን ዓበይት መመሪያዎች አንዱ ነው!” የሚለውን መርሁ አሳስቧል። #Ethiopia #southethiopia #kucazone