የዎላይታ ሶዶ ስታዲየም: ከስፖርት ማዕከልነት ባለፈ የከተማ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ሶዶ ሊገነባ የታቀደው አዲስ ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ ከተለመደው የስፖርት መድረክነት ባለፈ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት “ቢዝነስ ኢንተግሬትድ ስታዲየም” (BIS) እንዲሆን እየተጠየቀ ነው።

ይህ ጥሪ የቀረበው በታዋቂው የምጣኔ ሀብት አማካሪና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ማቴዎስ ባልቻ ሲሆን፣ ስታዲየሙ ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲታቀድ አሳስበዋል።

አቶ ማቴዎስ ባልቻ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የተገነቡ በርካታ ስታዲየሞች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸውና ለቢዝነስና ኢኮኖሚ ልማት ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ ሳያደርጉ መቅረታቸው፣ ኢንቨስትመንቱ ፍሬ አልባ እንዲሆን አድርጎታል።

“ከመነሻው የነበረው የእሳቤ ስህተት ነው” ሲሉ ይህንን አሠራር ይተቻሉ። የዎላይታ ሶዶ ስታዲየም ግን ከዚህ ስህተት ተምሮ የተሻለ መንገድ እንዲከተል አሳስበዋል።

BIS ሞዴል ምንድን ነው?

አቶ ማቴዎስ ባልቻ የ BIS ሞዴልን ሲያብራሩ፣ ሶስት ቁልፍ ነጥቦችን አስቀምጠዋል፦

  • የወጪ መመለስ (Return On Investment – ROI): ስታዲየሙ ለግንባታ የወጣውን ወጪ መልሶ በማስገኘት፣ ከሚያገኘው ገቢ ሌሎች አነስተኛ ስታዲየሞችንና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ለመገንባት የሚያስችል ገቢ ማመንጨት መቻል አለበት።
  • የኮሜርስ ማዕከልነት: ስታዲየሙ የስፖርት ውድድሮች የሚካሄዱበት ብቻ ሳይሆን፣ ሱፐር ማርኬቶችን፣ የችርቻሮ ሱቆችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን እና በርካታ አነስተኛና መካከለኛ ንግዶችን በማቀፍ የከተማዋ ወሳኝ የቢዝነስ ማዕከል መሆን አለበት።
  • ተመራጭ ስፍራ: ስታዲየሙ ከከተማው ዳርቻ ተነጥሎ ከመገንባት ይልቅ፣ በከተማው ውስጥ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በሚበዙበት ምቹ ቦታ በመምረጥ የከተማዋ ኢኮኖሚ ሞተር እንዲሆን ታሳቢ መደረግ አለበት።

ይህም ከቀደሙት ፕሮጀክቶች ልምድ በመውሰድ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው ሳይሰሩ የቀሩ ተቋማትን እጣ ፈንታ ለማረም ይረዳል።

የአፍሪካና ዓለም አቀፍ የ BIS ተሞክሮዎች
አቶ ማቴዎስ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የ BIS ሞዴልን በተሳካ ሁኔታ የተከተሉ ስታዲየሞችን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል፦

  • FNB ስታዲየም (ጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ): ከ400 በላይ ቢዝነሶችን ያቀፈ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ሞሎች እና ምግብ ቤቶችን ይዞ ለንግድ እንቅስቃሴ የሚውል።
  • ሞሰስ ማቢዳ ስታዲየም (ደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ): ከ250 በላይ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶችና የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያስተናግዱ አዳራሾች ያሉት፣ ሁልጊዜም ሞቅ ያለ የኢኮኖሚ ማዕከል ነው።
  • ካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም (ካይሮ፣ ግብፅ): የተለያዩ ውድድሮችን ከማስተናገድ ባለፈ የመዝናኛ፣ የንግድ ሱቆችና ሌሎች የንግድ ሥራዎች የሚካሄዱበት የከተማዋን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ማዕከል ነው።
  • ስታድ ዴ ማራካሽ (ማራካሽ፣ ሞሮኮ): ከ300 በላይ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና የተለያዩ ዝግጅቶችን ማቅረቢያ አዳራሾች ያሉት፣ ሁልጊዜም ሞቅ ያለ የኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።

ከአፍሪካ ውጭም የእንግሊዙ ቶትንሃም ስታዲየም የከተማውን እስከ 20% የሚሆነውን የቢዝነስ እንቅስቃሴ በመደገፍ በዓለም ላይ “the most business vibrant Stadium” ተብሎ እንደሚታወቅ አቶ ማቴዎስ ጠቁመዋል።

አነጋግሩን… እንነጋገር ጥሪ

በማጠቃለያው፣ አቶ ማቴዎስ ባልቻ የዎላይታ ሶዶ ስታዲየም ለከተማው ቢዝነስና ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት፣ ከከተማው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ፣ ኢንቨስትመንቱን በመመለስ ገቢ የሚያመነጭ እና ለተጨማሪ ተቋማት ግንባታ የሚያስችል ንቁ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆን አሳስበዋል።

ለዚህም የምህንድስና ባለሙያዎች የአርክቴክቸራልና ስትራክቸራል ዲዛይን እንደሚያቀርቡት ሁሉ፣ እንደ እሳቸው ያሉ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ልማት ባለሙያዎችም የስታዲየሙን ኢኮኖሚያዊና ቢዝነስ አዋጭነት (Economic & Business Feasibility) ጥናት በማድረግ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ማቴዎስ በነፃ ጥናት በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው፣ የሚመለከተው አካል እንዲያነጋግራቸው “አነጋግሩን… እንነጋገር” በማለት ጥሪያቸውን ደምድመዋል።

Ethiopia #Wolaita #southethiopia