1000063218

የዎላይታ ዲቻ ድል የበርካቶችን ልብ በደስታ ቢሞላም፣ ከዚህ አወዛጋቢ የፍርድ ሂደት በስተጀርባ ሊዘነጉ የማይገቡ በርካታ ነጥቦች አሉ። የፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦናን ትንታኔዎች ተንተርሰን፣ ከዚህ ድል ባሻገር የኢትዮጵያን እግር ኳስ የወደፊት ጉዞ የሚቃኙ ቁምነገሮችን እንመለከታለን።

  1. ግልጽነት የጎደለው የመንግሥት አሠራርና የኃላፊነት መዘናጋት

በመንግሥት በኩል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎችን ያለ በቂ ምክንያት በዝግ ስታዲየም እንዲደረጉ ማዘዙ ከባድ ስህተት ነው። አሳማኝ ምክንያት ቢኖር እንኳ፣ አገላለጹ በትህትና ተብራርቶ ለሕዝብ መገለጽ ሲገባው ያ አልሆነም። ይባስ ብሎ ጨዋታው ከተደረገ በኋላ ደጋፊው ባልተጋጨበት ሁኔታ፣ ግጭት ስለተፈጠረ ጨዋታው በዝግ እንዲደረግ ተወሰነ ማለት አሳፋሪ ውሸት ነው።

ሁለት ወንድማማች ክለቦችን ደጋፊዎች ተጋጩ ማለትም በጣም ያሳፍራል። መንግሥት የኢትዮጵያ ዋንጫን በስታዲየም ውስጥ ሰላም አስጠብቆ ማስፈጸም አለመቻሉስ አሳሳቢ አይደለምን? ከዚህም ባሻገር፣ አገር የሚጠብቀው የዋንጫ ጨዋታ በሚደረግባት አዲስ አበባ፣ መለያ የለበሰ ደጋፊ በየቦታው መታየቱ፣ መጨፈሩና መዝፈኑ ምንም ችግር ሳይኖረው፣ ወጣቶችን ማዋከብ፣ ማባረር፣ መምታትና በጅምላ ማሰር በጣም ወራዳ ተግባር ነው። ይህ በደጋፊው ላይ የደረሰው እንግልት ቡድኑንና ሕዝቡን በስነ-ልቦና ለመጉዳት ታስቦ የተሰራ ተራ ተንኮል ይመስላል።

ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከነበረው ጨዋታ በፊትም የቡና ደጋፊዎች ቀድመው ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተደርጎ፣ የዲቻ ደጋፊዎች ጨዋታው ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ እንዲገቡ መደረጉን፣ በቦታው ከነበሩ ሰዎች እንደሰማሁት፣ በወቅቱ በደሉ ምክንያት እስከ ማልቀስ የደረሱ ደጋፊዎች ነበሩ። ለማንኛውም ሕዝብን መጥላትም ሆነ መናቅ ዋጋ ያስከፍላል።

  1. የእግር ኳስ ዘርፍ የአመራር ውድቀት

ይህ ችግር ከፌዴሬሽኑ እስከ ክለቦቹ የሚዘልቅ ነው። ፌዴሬሽኑ ጨዋታው በድንገት በዝግ ስታዲየም እንዲደረግ ትዕዛዝ ሲተላለፍለት፣ የመንግሥትን ትዕዛዝ ማክበሩ ቢጠበቅም፣ ጨዋታውን ላልተወሰነ ጊዜ አለማራዘሙ ከባድ ውድቀት ነው።

“የሊግ ካምፓኒ” ተብዬውም እንቅስቃሴ እንዳላደርግና ውሳኔዎቼን እንዳላስፈጽም ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ወስደው ያገዱኝ የክለቦች አመራሮች ናቸው ማለቱ በቀላሉ መታየት የለበትም። የሲዳማ ቡና አመራር በፊፋ አሰራር የእግር ኳስን ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ማስዳኘት እንደማይቻል ማወቅ ነበረበት።

በተጨማሪም በመደበኛ ፍርድ ቤት በተወሰኑ ውሳኔዎች ተማምኖ ተጫዋቾችን ማሰለፉ የአመራር ውድቀት ነው። ኢሳያስ ጅራ የፋይናንስ ጨዋነት ምርመራው የሌሎች ክለቦች ምርመራ እንዳይቀጥል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱ ክለቦች እንቅፋት ሆነዋል ቢልም፣ ምላሹ አጥጋቢ አይደለም።

  1. የዳኝነት ሸፍጥና አቅም ማነስ

በጨዋታው ከቅጣት ምት ዎላይታ ዲቻ ያስቆጠረውን ንጹህ ግብ የመስመር ዳኛው ሲሽር፣ የመሐል ዳኛውም አሻሚ ያልነበረውን ግብ ሽሮ ጨዋታውን ማስቀጠሉ በጣም አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ የአምናውን የዳኝነት በደል በድጋሚ የሚያስታውስ ነው። በወቅቱ ጨዋታውን ያየ ገለልተኛ ደጋፊን ጨምሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጨዋታውን ያስተላለፉ ጋዜጠኞች ጭምር በዚህ ተስማምተው ነበር።

  1. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገምተኛነት

ወደ 60 ዓመታት ገደማ የቆየው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዛሬም እግር ኳስን የሚያሰራጭበት ጥራት አሳፋሪ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ዛሬ በየሰፈሩ ያሉ የቪዲዮ ቀረጻና ኤዲቲንግ ባለሙያዎች እድሉ ቢሰጣቸው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተሻለ ጥራት እንደሚያሰራጩ ግልጽ ነው።

ዲኤስቲቪ በኢትዮጵያ ያስጀመረው የስርጭት ጥራት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መልሶ ወደ ኋላ እንደከተተው ግልጽ ነው። የገንዘብ ችግር ከሆነ እንኳን፣ ቀድሞ ስፖንሰር አድርጉ ቢባል ከዎላይታና ሲዳማ አካባቢ ብዙ ድርጅቶች መሳተፍ ይችሉ ነበር።

  1. የፊፋ (FIFA) ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት የጸዳ ፍትሃዊ አሰራር

በተለይ ዝርክርክ የመንግሥትና የክለብ አመራሮች፣ እዚህ አገር ውስጥ የለመዱትን ሥርዓት አልበኝነትና ዝርክርክነት በእግር ኳሱ ላይ ለመድገም ካሰቡ፣ የፊፋ አሰራር ግምት ውስጥ ሳይገባ ኢትዮጵያን ከአለም አቀፍና አህጉራዊ እግር ኳስ እንቅስቃሴ ያግዳልና አደብ ቢገዙ መልካም ነው።

  1. የእግር ኳስ ስፖርት ቤተሰብ የሞራል ጉዳት

ሕዝብን መናቅ ትዝብት ላይ ይጥላል። በሂደቱ የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ የሞራል ጉዳት ደርሷል፣ ያም በጣም ያሳዝናል:: ሌላው የእግር ኳስ ቤተሰብም በሂደቱ በጣም አዝኗል።

ማጠቃለያ

ይህ በሁለቱም በኩል ሀዘንና ደስታን ያፈራረቀው ሂደት፣ የሁለቱ ቡድን ደጋፊና የስፖርቱ ቤተሰብ፣ በእውቀት አልባ አመራርና በዝርክርክ አሰራሮች ምክንያት እንዲሁም በሌሎች መንግሥታዊ ችግሮች የተፈጠረ ክስተት መሆኑን በመቀበል፣ በመተሳሰብና በመተዛዘን ማለፍ ይገባል።

በተለይም ወንድማማቹ የሁለቱ ክለቦች ስፖርት ቤተሰብ፣ እርስ በርስ የተበዳደለው ነገር ባለመኖሩ፣ በምንም መልኩ መናቆር የለበትም። አሁን የተገለጸውን ውጤት በመቀበል፣ ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ላይ መረባረብ አለበት። ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የWT ሚዲያ ተጋባዥ ጸሃፊ