1000063583

በትግራይ ጉዳይ የተጋለጠው አይነት የሕግ ክፍተት እና የፓርላማ ሥርዓታችን የወደፊት ፈተና በምን አግባብ ይፈታሉ ? “ህጉ አማራና ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ያሸነፈ ፓርቲ መንግስት እንዲመሰርት የሚፈቅድ አግላይ ነው” – የWT ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ባሉት 12 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም በ548 መቀመጫዎች በሚወከለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመራ ነው። ይሁን እንጂ፣ በቅርብ ጊዜ በተለይም በትግራይ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ፣ በሕግ አውጪው አካል ውስጥ ትልቅ ክፍተት መፈጠሩን የWT ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ የምትከተለው የፓርላማ ሥርዓት ያለበትን ተግዳሮት በግልጽ አሳይቷልም ብለዋል።

በትግራይ ክልል በሰላም እጦት ምክንያት ምርጫ ሳይካሄድ ሲቀር፣ የመላ አገሪቱ ምርጫ ተደርጎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሟል። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ወኪሎች መቀመጫ ባዶ ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ ደግሞ ክልሉ ወኪሎች ሳይኖሩት አገራዊ ሕጎችን የመተዳደር ግዴታ እንዲገባ አድርጎታል፣ ይህም ፍትሃዊነትን የሚጠይቅ ትልቅ የሕግ ክፍተት ነው።

የሕግ ክፍተቱ ምንነት

የኢትዮጵያ የፓርላማ ሥርዓት አንድ ፓርቲ መንግሥት ለመመሥረት 274 መቀመጫዎች ብቻ እንደሚያስፈልገው ይደነግጋል። የWT ሚዲያ ጸሓፊው ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ይህንን ሕግ ሲተነትኑ፣ “ይህ [ሕግ] አማራና ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ያሸነፈ ፓርቲ መንግስት እንዲመሰርት ከማስቻሉም በላይ አንድ ትግራይ ብቻ ሳይሆን በተቀሩ 10 ክልሎች ምርጫ በአንዳች ምክንያት ባይካሄድም እንኳን መንግሥት ከመመስረት አንድን ፓርቲ የማያግድ ኢፍትሐዊ ሕግ መሆኑ እሙን ነው” በማለት አስረድተዋል።

ይህ ሁኔታ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላው ኢትዮጵያ የሚተገበሩ ሕጎችን የማውጣት ሥራውን እንደቀጠለ ቢሆንም፣ የትግራይ ተወካዮች ወንበር ባዶ መሆኑ “ተወካዮች አይጠይቁም፣ አስተያየት አይሰጡም፣ ድምጽም አይሰጡም” ማለት ሲሆን፣ ክልሉ ግን ባልተወከለበት በሚወጡ ሕጎች የመተዳደር ግዴታ ሥር መሆኑን ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ይጠቁማሉ።

የወደፊት ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎች

ይህ የሕግ ክፍተት ወደፊት ሌሎች ክልሎችንም ሊያጋጥም እንደሚችል ማሪንዶስ ጦና አስጠንቅቀዋል። በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በመጥቀስ፣ በድርድር ሰላማዊ እልባት ካልተገኘ በሚቀጥለው ዓመት አገራዊ ምርጫ በክልሉ እንዲካሄድ አስቻይ ሁኔታ ላይኖር እንደሚችል ገልጸዋል።

“አገሪቷ በዚህ የነውጥ መንገድ ከቀጠለች አሁን ትግራይን የገጠማት ችግር በአማራ ክልልም የሚደገምበት እድል አለና ከወዲሁ መፍትሔ ቢፈለግ ይበጃል” ብለዋል።

እንደ መፍትሄ ሃሳብ፣ በትግራይ ክልል ለምሳሌ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ፣ የፌዴራል መንግሥቱ የግዛት አንድነትን አረጋግጦ የማሞያ ምርጫ እና የDDR (Disarmament, Demobilization, and Reintegration) ሂደቶችን በማካሄድ ክፍተቱን መሙላት ይችል እንደነበር ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ፣ በኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ ተካሂዶ የፖለቲካ ድርድርም ታክሎበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ድልድሉ መሻሻል እንዳለበት ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል።

በተጨማሪም፣ አሸንፎ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስፈልገው የወንበር ቁጥር ከፍ መደረግ እንዳለበት፣ አለያም የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን የሚቀነስበት መፍትሔ መምጣት እንዳለበትም ፕሮፌሰር ማሪንዶስ በጽሑፋቸው አብራርተዋል።