GridArt_20250710_202944519

“የህዝብ ድምፅ ለማሰማት የተቀጠሩ ጋዜጠኞች ከተቋሙ በሚደርሰው ማስፈራሪያ ምክንያት የራሳቸውን በደል እንኳን መናገር አልቻልንም” ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

WT ሚዲያ በደረሰው መረጃ መሠረት፣ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ደሬቴድ) ሰራተኞች በተለይም ከደመወዝ ክፍያና ከስራ ዋስትና ጋር በተያያዘ ከባድ ስጋትና ቅሬታ እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የድርጅቱ ሰራተኛ ለWT ሚዲያ በላከው መልዕክት፣ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የደቡብ ክልል ሳይከፋፈል በፊት ለሰራተኞቹ የወር ደመወዝ በወቅቱ ይከፍል እንደነበር አስታውሷል።

በአሁን ወቅት ግን የሰኔ ወር ደመወዝ ሳይከፈል የበጀት ዓመቱ መገባደዱን ገልጿል።

ከዚህም ባሻገር፣ መንግስት ከዚህ በፊት የሰራተኛ ደመወዝ ማስተካከያ ባደረገበት ወቅት ለደሬቴድ ሰራተኞችም ማስተካከያው እንደተደረገላቸው የገለጸው ይኸው ሰራተኛ፣ የ5 ወራት የ”back payment” ክፍያ መንግስት በጀቱን ቢሰጥም በአሁኑ ወቅት ተቋሙን እየመራ ያለው አካል ለመክፈል ፍቃደኛ እንዳልሆነ አስረድቷል።

በተጨማሪም፣ ጋዜጠኞች መብታቸውን እንዳይጠይቁ የማስፈራራትና የማገድ ተግባር ስለሚፈጸምባቸው ዝምታን እንደመረጡ የጠቆመው ምንጩ፣ የድርጅቱም የመጨረሻ እጣ ፈንታና ህልውናው እስካሁንም ግልጽ አለመሆኑን በመግለጽ ስጋቱን አሰምቷል።

WT ሚዲያ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
#Ethiopia #southethiopia #ደሬቴድ