የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕረዚዳንት በህዝብ ላይ እያደረሰ ባለው ሰብዓዊ መብት ጥሰትና እየፈጸመ ባለው በተደራጀ ሌብነት ምክንያት ከቦርድ አባልነት መልቀቃቸውን አሳወቁ።
በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የጋሞ ልማት ማህበር ቦርድ አባል የሆኑት የህግ ባለሙያ አቶ ደሳለኝ ከበደ ካዛ፣ ከጋሞ ልማት ማህበር ቦርድ አባልነት ራሳቸውን እንዳገለሉ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን WT ሚዲያ ተመልክቷል።
አቶ ደሳለኝ ይህንን ውሳኔያቸውን ከ10 ዋና ዋና ምክንያቶች ጋር በማያያዝ በዝርዝር አስቀምጠዋል።
አቶ ደሳለኝ እንደገለጹት፣ ህዝብ እና መንግስት ከቦርድ አባልነት ራሳቸውን ያገለሉባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች የማወቅ መብት ስላላቸው፣ በሚቀጥሉት ቀናት እያንዳንዱን ነጥብ በዝርዝር ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
አቶ ደሳለኝ ቦርዱ በወሰነው መሰረት፣ በአቶ ጥላሁን ከበደ ቀጥተኛ ትእዛዝ፣ አንባገነናዊ ውሳኔ እና የሙስና ተግባር ከ200 ሄክታር በላይ የአርባምንጭ እርሻ ልማት ድርጅት መሬት ለልዩነህ ዱባሌ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ እና ለጥቂት ግለሰቦች በቢሊዮን ብሮች መተላለፉን ጠቁመዋል።
ይህ ተግባር ተቋሙን አደጋ ላይ እየጣለ በመሆኑ ህዝቡ ተቋሙን እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።
የልማት ማህበሩ የሰው ሀብት አስተዳደር መመሪያ ተጥሶ፣ በአቶ ጥላሁን ከበደ ቀጥተኛ ትዕዛዝ፣ የወንጀል ሪከርድ ያለባቸው፣ ጡረታ የወጡ እና ከመንግስት ተቋማት ከኃላፊነት የተነሱ ግለሰቦች ተቀጥረው የሀብት ብዝበዛ እየፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
አቶ ጥላሁን እና አቶ አዋሽ የሚባሉ ግለሰቦች ከ15 ዓመት በላይ በቦርድ አባልነት መቆየታቸው ህገወጥ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።
የቦርድ አባልነት ቢበዛ ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ መሆን ሲገባው፣ አቶ ጥላሁንን ጨምሮ ከ25 ዓመት በላይ የግል ቤት ያደረጉ ግለሰቦች መኖራቸው ለከፍተኛ የጥቅም ትስስር እና ብልሹ አሰራር መራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ስራ አስፈጻሚ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በኃላፊነት መቆየቱ እና የባንክ አካውንት ፈራሚ መሆኑ የጥቅም ግጭት እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ይህንን ለማስተካከል ያቀረቡት ሀሳብ ችላ መባሉን አብራርተዋል።
ቅርንጫፉ ሆን ተብሎ ሪፎርም ሳይደረግ በመቆየቱ ምክንያት የቀድሞ ሁለት የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች ስራ እንደለቀቁም ጠቁመዋል።
አቶ ደሳለኝ ሰላም ማይክሮ ፋይናንስ እንዳይመሰረት አቶ ጥላሁን ከበደ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በግፍ ለተፈናቀሉ የጋሞ ተወላጆች መብት ለማስከበር እና በጋሞ ቆላማ አካባቢዎች በዘላቂነት ለማደራጀት ፕሮጀክት ቀርቦ ጥረት ቢደረግም፣ አቶ ጥላሁን ከበደ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ህዝቡ እየተሰቃየ መሆኑን ገልጸዋል።
አንድ የቦርድ አባል በተለይም አቶ ጥላሁን ከበደ ከሁሉም በላይ ሆነው ተቋሙ እንዳያድግ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸው፣ የጋሞ ህዝብን እንደ መያዣ በመጠቀም የማስመሰል ወጫታ እየተጫወቱ ነው ሲሉ ከሰዋል።
በጋሞ ዞን በተለይ በሻራ እና ዘይሴ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች እና ንጹሃን ዜጎች በግፍ እንዲገደሉ አቶ ጥላሁን ከበደ እጅ እንዳለበት ጠቁመዋል።
በህገ-መንግስታዊ ስርዓት ላይ ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በፈጠራ ክስ የተከሰሱ ንጹሃን ግለሰቦች ከግድያው ጀርባ እጃቸው የሌለበት መሆኑን እና ከነፃ መውጣታቸው በኋላ “ምህረት አደርግላችኋለሁ” ተብለው እንዲቀጡ የተደረገው ድራማ እንደሆነ በመግለጫቸው አስፍረዋል።
በጋሞ ዞን በፖሊሶችና የፖለቲካ አመራሮች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ብልሹ አሰራሮች እና የግፍ ግድያዎችን ለማስቆም የቀረበ ሀሳብ “ህግ ሳይሆን ፖለቲካ ነው የማገዛው” በሚል ውድቅ መደረጉን ገልጸው፣ አቶ ጥላሁን እና መሰሎቻቸው ህዝቡን ለማሰቃየት እየሰሩ ነው ብለዋል።
ልማት ማህበሩ ላስመዘገባቸው ስኬቶች ሚና የነበራቸውን የቦርድ አባላት (ለምሳሌ እጩ ዶ/ር ወንድማገኝ ታዬን) ያለ ምንም ምክንያት ከቦርድ አባልነት ማሰናበት፣ ለወራት ያለምንም ክፍያ አገልግለው ስራ የለቀቁትን የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አቶ ትግሉ ሃይሌን እውቅና መንፈግ፣ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ ከስራ የተባረሩትን አቶ ተካልኝ ተፈሪን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን በመጥቀስ ብቃት ያላቸው አመራሮች እየተገፉ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ደሳለኝ ማህበሩ በትውልድ ቅብብሎሽ የተሻለ ማደግ እንዳለበት በመግለጽ፣ የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው እና የጥቅም ግጭት የሚፈጥሩ ሁሉም የቦርድ አባላት ብቃት ባላቸው አባላት መተካት እንዳለባቸው ቀደም ሲልም በጽሁፍ ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል።
በተለይም የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አቶ ትግሉ ሃይሌ ከለቀቁ በኋላ የተፈጠሩት አሳሳቢ ሁኔታዎች እየተባባሱ በመምጣታቸው ይህንን ውሳኔ ለመውሰድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ ግለሰባዊ ጥቅምን ከማሳደድ ይልቅ የህዝብ ጥቅም በዘላቂነት እንዲከበር ጠንካራ መሰረት መጣል አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
ተቋሙ ከታደሰ እና ከተፈወሰ በላቀ ተነሳሽነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ደሳለኝ “ክፉዎች ህዝቤን ማሰቃየት አይችሉም! የህግ የበላይነት፣ ፍትህ፣ መልካም አስተዳደር እና ልማት ምን እንደሆነ እስኪገባቸውና ህዝባችን ጫንቃ ላይ የጫኑትን የስቃይ ቀንበር እስኪያነሱ ድረስ አልተዋቸውም!!!” በማለት በመግለጫቸው አክለዋል።
እንደሚታወቀው WT ሚዲያ በተደጋጋሚ ከላይ የተነሱ ጉዳዮች ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አማካይነትና እየተካሄደ የሚገኘውን የሌብነት፣ የአድልዎ አሰራር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ኢፍትሃዊነት፣ ከህግ በላይ ስልጣንን መጠቀም እንዲሁም ሌሎች ተጨባጭ ብልሹ አሰራሮችን በሰነድ አስደግፈን በየቀኑ ለህዝብ ይፋ እያደረግን እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።
በመሆኑም በዛሬው ዕለት የርዕሰ መስተዳድሩ አከባቢ ተወላጅ እንዲሁም ስራዎችን በቅርበት ለረጅም ጊዜ እየሰራ የነበሩት ግለሰብ ወደ ህዝብ ያጋለጡት መረጃ የሚዲያችን እውነተኝነትና ለተበደለው ማህበረሰብ የምናደርገው የመረጃ አብዮት ሀቅ ያስመሰከረ ነውና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አፋጣኝና ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ እናቀርባለን።
“ጥ