ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ትኩረት እንዲሰጡ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ጥሪ አቀረቡ።
የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ የጀመረ ታላቅ ሰነድ መሆኑን የWT ሚዲያ ተጋባዥ ጸሃፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና አበክረው አሳስበዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ገለጻ፣ የስምምነቱ ፋይዳ ግጭትን ከማስቆም ባለፈ ፍጅትንና የሞራል፣ የመርህ እና የሕግ አልባ አካሄዶችን የገታ ነው። ከዚህም ባሻገር፣ የተለያዩ ተፋላሚ ኃይሎች የመንግስትን ስልጣን በድርድር የሚጋሩበትን አቅጣጫ ያስቀመጠ ታሪካዊ ሰነድ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ማሪንዶስ፣ ይህ ስምምነት ሀገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣት ፋታ የሰጠ ትልቅ የፖለቲካ እርምጃ እንደሆነ አብራርተዋል።
ስምምነቱ በየትኛውም ወገን ቢፈርስ፣ ብዙ መዘዝ የሚያስከትልና መጨረሻውን ለመገመት እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ለዚህም ብልጽግና ፓርቲንም ሆነ ህወሃትን ስምምነቱን በመፈረማቸው አመስግነዋል።
ብልጽግና ጦርነቱን ማስቆም እየቻለ ለሰላም ቁርጠኛ በመሆኑ እንደተፈራረመ ሲገልጽ፣ ህወሃት ደግሞ ስምምነቱ የተመረጠውን የክልሉን መንግስት የሚያፈርስ በመሆኑ ቅሬታ ቢኖረውም፣ በሙላት ቢተገበር ጥሩ ነው ማለታቸውን ፕሮፌሰሩ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም ወገኖች የሚሰጡት ምክንያት ስህተትና ጠቃሚ እንዳልሆነ ፕሮፌሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
“ብዙ ሰዎች የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚተቹት ግጭቱ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ አካላትን ያላሳተፈ በመሆኑ ነው። ነገር ግን ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ይህ የስምምነቱ አንዱ ጠንካራ ጎን እንደሆነ ያምናሉ። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ሰምሃል፣ ስምምነቱ ከጅምሩ Bilateral (ሁለትዮሽ) ሳይሆን Multilateral (ባለብዙ ወገን) መሆን ነበረበት በማለት፣ የተለያዩ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ሊሳተፉበት ይገባ ነበር” ብለዋል።
“ይሄም ምላሽ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት የተነሱት የቀድሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ከሪፖርተር ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ጋር ተቀራራቢ ነው። በተጨማሪም ለአለም ባንክ ፕሬዝዳንትነት ከመወዳደር በጥቁርነቱ መገፋቱ የተወራለት ዶክተር ዮናስ ብሩምም ይህንኑ ነጥብ አንስተዋል። ሆኖም ግን፣ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ የሶስቱም ወገኖች ነጥብ ተገቢ እንዳልሆነ” ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸዋል።
የWT ሚዲያ እንግዳ ፀሐፊ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ፣ ብዙ ሰዎች ስለ ትግራይ ጦርነት የተሳሳተ ግንዛቤ ከሚይዙባቸው ነጥቦች አንዱ የሕግ ማዕቀፍ ሲሆን ሁለተኛው ስለጦርነቱ መነሻ ያለው የተዛባ ግንዛቤ እንደሆነ ያምናሉ።
የፕሪቶሪያ ግጭት ማቆም ስምምነት እንደ ፖለቲካ ነክ የሕግ ሰነድ መተግበር የሚችል መሆኑ ተገቢ ሆኖ፣ ስምምነቱ በአለም አቀፍ ታዛቢና አደራዳሪዎች ፊት በተደረገ ድርድር መምጣቱን ማወቅ ያስፈልጋል ይላሉ።
በዚህ ሂደት፣ ሕግና ስርዓት ወደነበረበት ይመለስ ሲባል፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በጦርነቱ የሻዕቢያ ጣልቃ ገብነት ስህተት የነበረ መሆኑ ግልጽ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
በመቀጠል ደግሞ “የአማራ ክልል ከሀገሪቱ ህገ መንግስት ውጪ በሃይል ከተቆጣጠረው ግዛት ይውጣ መባሉም የአደባባይ ሚስጢር ነው። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት እነዚህ በጠራራ ጸሐይ ሲፈጸሙ የነበሩ የእብደት እርምጃዎች መሞገት እንኳን የማይቻልበት ነበረ። እነዚህ ሁለቱ ድርጊቶች የፌደራል መንግስት ካለው የሕግ ማስከበር ማዕቀፍ ውጪና በተለይ በትግራይ በኩል ጦርነቱ ህዝባዊ እንዲሆን ትልቅ ሚና የነበራቸው ነገሮች ናቸው” በሚል ይሞግታሉ።
ስለዚህ ማንኛውም ፍትሃዊ አደራዳሪ እነዚህን ሁለት ግልጽ በደሎች ለትግራይ ሕዝብ ያለምንም ማንገራገር መፍረዱ የሚጠበቅ ነው። ሌላው በአማራ ክልል ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ፋኖ የሚባል ደባል ኃይል መደራጀቱ ስህተት ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ ሌላ ግጭት ሊፈጥር የሚችል ነገር መሆኑም ተገማች ነበር ብለዋል ፕሮፌሰር ማሪንዶስ።
የፌደራል መንግስትና የአማራ ክልል መንግስት በዚህ ተጠያቂ መሆናቸውንና ችግሩንም ለመፍታት ሰጥተው ለመቀበል መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋኖና የኦነግ ግጭት ከክልል መንግስታት ጋር ብቻ ማያያዙ የተሳሳተና ሰላምን የሚያርቅ አባባል ነውና መታረም እንዳለበት አሳስበዋል።
ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት ስንመለስ፣ ሉዓላዊነት የሚከበርበት አቅጣጫ የተቀመጠበት፣ ህገ መንግስታዊነት እንዲሰፍን ስምምነት የተደረሰበት፣ ትግራይ የፌደሬሽኑ አካል እንደመሆኗ ሚዛናዊ ውክልና እንዲረጋገጥ አቅጣጫ የተቀመጠበት ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ አስረድተዋል።
ይህ ስምምነት ለሀገራችን እንግዳ ከመሆኑም በላይ ሀገር ከገባችበት የተሳሳተ አካሄድ የምትመለስበትን አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው። ይህ ግጭት የማቆም ስምምነት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ምልአተ ህዝቡ አስፈላጊነቱን ተረድቶ፣ በሁለቱም በኩል ተፈጻሚ እንዲሆን ጫና ማሳደር እንዳለበት ተማፅነዋል።
አለም አቀፍ አካላትም፣ በተለይ የአፍሪካ ህብረት ይህ የተስፋን ብርሃን የፈነጠቀው የግጭት ማቆም ስምምነት እንዳይፈርስ፣ በተለየ ትኩረት መስራት አለበት፤ የስምምነቱ አተገባበርም ያለበት ደረጃ በጋራ እንዲገመገም ማድረግ እንዳለበት በመጠቆም የትግራይ ጦርነት እጅግ አሰቃቂና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የጎዳ መሆኑን ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ንግግራቸውን አጠናቀዋል።