GridArt_20250805_171206479

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ባሉ የተለያዩ ዞኖችና ብሔረሰቦች መካከል ከክልሉ አመራር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቅሬታና ውጥረት እየተፈጠረ መሆኑ ተዘገበ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የሚመሩት አስተዳደር፣ በልማት በጀት አመዳደብ እና በኢ-ፍትሃዊ የተቋማት ድልድል ምክንያት በበርካታ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ እያስነሳ ነው።

ይህ ሁኔታ በ2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ትልቅ አደጋ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋትም ተንጸባርቋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብቸኛው ህብረተሰቡ በአመራሮች እየደረሰ ባለው ከፍተኛ በደል የተነሳ ብልፅግና ፓርቲውን በመጥላት አብዛኞቹ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲ በመምረጥ ለክልልና ለፌደራል ፓርላማ ተወካዮቻቸውን መርጦ ካስገቡ ዞኖች አንዱ ጋሞ ዞን እንደሆነ ይታወቃል።

የዎላይታ ታይምስ (WT) ሚዲያ ባደረገው ዳሰሳ፣ የክልሉ አመራር በተለይ በዎላይታ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ፣ በአሪ፣ በደቡብ ኦሞ እና በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ “በረቀቀ ዘዴ በደል እየፈጸመ ነው” በሚል በምሁራን፣ በወጣቶችና በገበሬዎች ዘንድ እየተነጋገረበት ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከአቶ ብርሃኑ ዘውዴ ጋር በመተባበር የሚያደርጉት ድብቅ በደል “ከጀርመኑ የናዚ ስርዓት ጋር የሚወዳደር ጭካኔ የተሞላበት” ነው ተብሎም ተነቅፏል።

አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ ሁለት አመት ቢሆንም፣ ክልሉን በሚያስተዳድሩት አካላት ላይ የቅሬታ መአት እየጎረፈ ነው። በተለይም ተቋማትን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ማከፋፈላቸው፣ የዞኑን ህዝብ ፍላጎትና አቅም ያላገናዘቡ ውሳኔዎች ማሳለፋቸው፣ እንዲሁም ቀደም ሲል በክላስተር ከተሞች ተዋቅረው የነበሩ ቢሮዎችን መዝጋታቸው ህዝባዊ ተቃውሞ አስነስቷል።

በርካታ ነዋሪዎችና ምሁራን፣ ይህ አካሄድ በክልሉ ውስጥ ያለውን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የህዝቡን እኩል የመልማት ጥያቄ ካልተመለሰና የብልጽግና ፓርቲ አመራሩ ላይ እርምጃ ካልወሰደ፣ በ2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ “በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ አደገኛ እጣ ፈንታ ይገጥመዋል” የሚል ግምትም ከወዲሁ ተሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም በነበረው የደቡብ ክልል አስተዳደር ወቅትም ሆን ተብሎ ልማትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲገታ መደረጉ አሁንም በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እየተደገመ ነው የሚል ክስ ቀርቧል።

የተለያዩ የክልሉ ዞኖች ነዋሪዎች ለዎላይታ ታይምስ በላኳቸው መልእክቶች፣ በጭቆና ላይ የተመሰረተ አብሮነት እንደማይቀበሉ፣ የህዝቡ የእኩል የመልማት መብት እንዲከበርላቸው፣ እንዲሁም ችግር ፈጣሪ አመራሮች የመፍትሄ አካል መሆን ስለማይችሉ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባላቸው ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ከዚህ በፊት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በቁጫ እና ዛይሴ ህዝቦች ላይ ባደረሰው ኢፍትሃዊነት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጭቆና ማድረሱን ተከትሎ ህዝቡ ገዢው ፓርቲው በአከባቢያቸው እንዳይመረጥ በማድረግ የራሳቸውን ተወካዮችን ለፓርላማ እና ለክልል ምክርቤት ማስመረጣቸው ይታወቃል።