GridArt_20250805_190313315

8 የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ በባህር ላይ ሰጥመው ሕይወታቸውን ላጡ ስደተኞች የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ፣ ችግሩን መፍታት የሚቻለው ሥርዓታዊ ለውጥ ሲመጣ ብቻ መሆኑን አስታወቀ።

ኮከሱ ባወጣው የሐዘን መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አሁን በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ዜጎችን ለአደገኛ ስደት እየዳረገ እንደሆነ በላከልን መግለጫ አስረድተዋል።

አክለውም “በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ላለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ መፍትሔ እንዲገኝ ህብረተሰቡ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ትግል መጀመር አለበት” በሚል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በባህር ላይ ሰጥመዋል ብሎ ከዘገባቸው 154 ስደተኞች አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የገለጸው ኮከሱ፣ ከቁጥሩ በላይ አሳሳቢው የችግሩ ሥረ-መሰረት መሆኑን ጠቅሷል።

በመግለጫው ላይ ኮከሱ “ዜጎች በነገአቸው ላይ ብሩህ ተስፋ እስካልታያቸው፣ ወጣቱ በትምህርቱና በቀጣይ ህይወቱ ከብሩህ መጻኢ ዕድል ይልቅ ድቅድቅ ጨለማ ከታየውና በአገሩ ተስፋ ከቆረጠ ይህ መርዶ ነገም የሚቀጥል ነው” ብሏል።

ስለሆነም ይህ ዓይነቱ አሰቃቂና ተደጋጋሚ እልቂት እንዲገታ፣ አሁን ያለው ሥርዓት በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ትግል መቀየር እንዳለበት ኮከሱ ለWT ሚዲያ በላከው አጭር መግለጫ ጠቁሟል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ በመጨረሻም መንግሥት የሐዘን ቀን እንዲያውጅ፣ ለሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ውይይትና ድርድር ዝግጁ መሆኑን እንዲገልጽ አልፎም የሽግግር ሂደት እንዲጀምር በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ስም ጠይቋል።

የሐዘን መግለጫውን ካወጡት ፓርቲዎች መካከል ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)፣ ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር ኢትዮጵያ)፣ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት (አረና)፣ ኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ መላው ሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መሲህዴፓ) ይገኙበታል።