1000068975

የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ያለው የክረምት መምህራን ስልጠና መቋረጡን አሳውቋል።

መግለጫው ይህ መቋረጥ የመጣው በመምህራኑ የሐምሌ ወር ደሞዝ መዘግየት፣ የውሎ አበል ክፍያ አለመፈጸም እንዲሁም ደካማ የመማርና የመኖር ሁኔታዎች ምክንያት እንደሆነ ለWT ሚዲያ በላከው ጠቅሷል።

በመግለጫው መሰረት፣ ስልጠናው ከዚህ ቀደም በነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. መምህራኑ በደመወዝ ክፍያና በኑሮ ሁኔታዎች ምክንያት ስራቸውን ካቆሙ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በኩል ችግሮቹ ይፈታሉ በሚል ቃል ተገብቶላቸው እንደገና ተጀምሮ ነበር።

ይሁን እንጂ የገቡት ቃል ባለመፈጸሙ፣ ማለትም ደመወዝ አሁንም ያልተከፈላቸው መምህራን በመኖራቸው፣ የውሎ አበል ክፍያ ባለመከናወኑ እና የመኝታ፣ የውሃ፣ የመፀዳጃ ቤትና የምግብ ጥራት ላይ ምንም ለውጥ ባለመደረጉ መምህራኑ በድጋሚ ነሐሴ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ስልጠናውን አቋርጠዋል።

የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የመምህራኑ ጥያቄዎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑ ጠቅሶ፣ ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለክልሉ መንግስት እና ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የተሰጡትን ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ መምህራንን ደመወዝ እንዲከፍሉ፣ እና የመምህራንን ደህንነት እና ክብር እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል።

ንቅናቄው መንግስት በስልጠናው ላይ ያፈሰሰው ውስን ገንዘብ ተገቢውን ውጤት እንዲያመጣ እነዚህ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል።