ለመሆኑ የኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በጋሞ ዞን ምን አላቸው ?
እንደሚታወቀው የፌደሬሽን ምክርቤት በሀገሪቱ ከብሄር ብሄረሰቦች መብት፣ ማንነት ጥያቄ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራ ቢሆንም በተቃራኒው የዚህ ተቋም መሪ የሆኑት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብሄር ብሄረሰቦች በማንነታቸው ምክንያት ስቃይ እየደረሰባቸው ወደ ሚገኙበት ዞን በተደጋጋሚ እየመጣ ከስራቸው በማይገናኙ ጉዳዮች ላይ ከአከባቢው አመራሮች ጋር በተደጋጋሚ መታየት የተለመደ እየሆነ ነው።
ለመሆኑ የፌደሬሽን ምክርቤት አፌ ጉባኤ ሆኖ በአከባቢው ብሄር ብሄረሰቦች በማንነታቸው ምክንያት ለሞት፣ ለእስር፣ ለስደት፣ ለውርደትና ለዘመናዊ ባርነት ተዳርገው የሚሰማ ህግ አጥቶ ከፈጣሪ ምላሽ በሚጠብቁበት ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞንና አከባቢው ላይ እየተመላለሰ ምን እየሰራ ይሁን የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ከሆነ ቆይቷል።
አፈጉባኤው በተደጋጋሚ በሚመላለስበት አከባቢ ላይ በማንነታቸው ምክንያት የጋሞ ዞን አመራሮች በቁጫ ብሔር ተወላጆች ላይ ለተከታታይ አካላዊ ድብደባ፣ እስራት፣ የገንዘብ ቅጣት፣ ከሥራ ማፈናቀል እና ከአካባቢው ዜጎችን በማሳደድ አያሌ መከራዎችን በሕዝብ ላይ በማድረስ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ በሚኖሩት የዛይሴ ብሔረሰብ ላይ በማንነታቸው ምክንያት በክልሉ ልዩ ኃይልና በጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊሶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈፀም፣ ግድያ እና የንብረት ውድመት እየደረሰ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ WT ሚዲያ እየዘገበ ይገኛል።
WT ሚዲያ ከታማኝ ምንጭ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የፌደሬሽን ምክርቤት አፌ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የብሄር ብሄረሰቦች ማንነት እውቅና እንዳያገኝ በተለይም በጋሞ ዞን እስከ ሀገሪቱ ፓርላማ ተወካዮች አንደበት እየተሰማ ያለው የቁጫ፣ የዛይሴ፣ የዶርዜ እና የሌላቸው በማንነታቸው ምክንያት እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ፣ እስር፣ እንግልት እና የንብረት ውድመት እየሰሙ ዝምታ የመረጡበት መንገድ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም በማግኘቱ እንደሆነ አስረድተዋል።
የእነዚህ ብሄሮች ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኝ አንዳንድ የጋሞ ዞን አመራሮች በተለይም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለአፌ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በአርባምንጭ ከተማ መሬት፣ በዛይሴ ብሄር ይዞታ ላይ ሰፊ የእንቨስትመንት መሬት፣ በየጊዜው ከፍተኛ ገንዘብ ከመንግሥት ካዝና አውጥቶ መስጠት እንዲሁም ወደ አከባቢው በሚመጣበት ወቅት የተለየ አቀባበል ማድረግ እንዲሁም ሲመለስ ቅቤና፣ ፍየል፣ በግ ስጦታ እንደሚበረከትላቸው ገልጸዋል።
እንደሚታወቀው አምና 19ኛው የብሄር ብሄረሰቦች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባለበት እንዳይከበር ተከልክሎ ለአፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር 10 ሚሊዮን ብር ጉቦ በመስጠት ብሄር ብሄረሰቦች ታፍነው በሚኖርበት በዚሁ አከባቢ ለገፅታ ግንባታ ተብሎ እንዲከበር መደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ ገዢ በማጣት ተመሳሳይ በዓል በማዕከላዊ ክልል ዋና መቀመጫ ሆሳዕና ከተማ እንዲከበር ከሞት የተረፉት አቶ አገኘው ተሻገር መግለጫ ሲሰጥ ተመልክተናል።
ከዚህ በሻገር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርዕሰ መስተዳደሩ ኢፍትሃዊነት ምክንያት ከፍተኛ ቅሬታ እየተሰማ ሲሆን በክልሉ ክላስተር ከተሞች ላይ የመንገድ፣ የንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የመስኖ ግንባታ፣ የጤና፣ የኤሌክትሪክ፣ የድልድይ እና የቴሌኮም አገልግሎትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታ ጥያቄዎች በተመለከተ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ትኩረት ካልተሰጠ አደገኛ ሁኔታ መኖሩ እየተሰማ ይገኛል።