“ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን በክልሉ እየተስተዋለ ባለው ኢፍትሃዊነትና ብልሹ አሰራሮች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ማግኘት አልቻልንም” – ሲሉ በክልሉ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች አባላት ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላትና የክልሉ ም/ቤት አባላት ከወከላቸው ህዝብ ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አረጋግጧል።
በዚህ ምክክር መድረኮች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች አባላት ጠንካራ በተወከሉባቸው አካባቢዎች በሚያደርጉ የመግባቢያ መድረኮች ውይይት እየተካሄደ የሚገኝ ቢሆኑም ከዚህ በፊት የተጠየቁ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ያለመሰጠታቸው ስማቸውን ለመጥቀስ ያልፈለጉ አንድአንድ ተወካዮች ጠቁሟል።
በክልሉ የጋራ የመልማት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እየተሻከረ እንደሚገኝ ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ለዚህም ምክንያት ሙሉ በጀትና የልማት ስራዎች ለአንድ ወገን ያደላ እንደሆነ አረጋግጠናል ይላሉ።
የኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች መቀመጫ ከሆነው አዲስ አበባ አርባምንጭ ከተማ ስንደርስ ይላሉ፤ አርባ ምንጭን ጨምሮ በጋሞ ዞን የሚገኙ ወረዳና ከተሞች ልማት ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ስነጻጸር ነገሩ ኢፍትሃዊነት የጎደለ እንደሆነ በቂ ማሳያዎች እንዳሉ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አስተያየትና ጥቆማ ሰጪዎቹ በቀጣይ እነዚህ ኢፍትሐዊ አካሄዶች ላይ እርማት ካልተወሰደ በቀድሞ ደቡብ ክልል እየተካሄደ የነበሩ አድሎዎች የአንድ አከባቢና ቡድን የበላይነት በአዲሱ ኢትዮጵያ ክልልም እየተጸባረቀ እና በአደባባይ እየተደገመ እንደሆነ በማንሳት በዚሁ አካሄድ ምክንያት ክልሉ የመፍረስ አደጋ መጋረጡንም ስጋታቸው አጋርተዋል።
አንድአንድ በተጨባጭ እየቀረቡ ያሉ የውሸት ሪፖርቶች ደግሞ ሌላኛው ጥቆማ ሲሆን በየወሩ ለፌዴራል መንግስት በክልሉ መንግስት ስር ያሉ ክላስተር ከተሞች እኩል እየለማ በሚል የውሸት ሪፖርት እንደሚቀርብ፣ ያልተሰሩ ስራዎችና ኘሮጀክቶች ተሰርቷል ማለት በዚህም የመንግስት ሚዲያዎች የሚሰጣቸው የውሸት ሪፖርቶች ይዘው ዜና በመስራት ለሙያ ክብር ሳይጨነቁ ከካድሬዎች በጥቅም እየተሳሰሩ በህዝቡ ላይ ቀልድ መያዙ ነው በጥቆማቸው ያነሱት።
ለዚህም በቀጣይ የፌዴራል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዉስጥ እየሆነ ያለው ነገር እያወቀ ዝምታ ከመምረጥ መፍትሄ ልሰጥ እንደሚገባ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያነጋገራቸው የተለያዩ አካባቢ የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች መረጃውን ሰጥተዋል።
በሌላ መልኩ በተደጋጋሚ ከህዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለምላሽና ማብራሪያ እንደማይገኙ የጠቆሙት ተወካዮቹ በግልጽ በህዝብ ቀልድ መያዙን ነው ያብራሩት።
እንደሚታወቀው WT ሚዲያ በተደጋጋሚ ከላይ የተነሱ ጉዳዮች ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አማካይነትና እየተካሄደ የሚገኘውን የሌብነት፣ የአድልዎ አሰራር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ኢፍትሃዊነት፣ ከህግ በላይ ስልጣንን መጠቀም እንዲሁም ሌሎች ተጨባጭ ብልሹ አሰራሮችን በሰነድ አስደግፈን በየቀኑ ለህዝብ ይፋ እያደረግን እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ከዚህ በሻገር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርዕሰ መስተዳደሩ ኢፍትሃዊነት ምክንያት ከፍተኛ ቅሬታ እየተሰማ ሲሆን በክልሉ ክላስተር ከተሞች ላይ የመንገድ፣ የንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የመስኖ ግንባታ፣ የጤና፣ የኤሌክትሪክ፣ የድልድይ እንዲሁም ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታ ጥያቄዎች በተመለከተ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ትኩረት ካልተሰጠ አደገኛ ሁኔታ መኖሩ እየተሰማ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
በመሆኑም ይሄው አሁን ደግሞ በክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላትና የክልሉ ም/ቤት አባላት፦ የርዕሰ መስተዳድሩን ኢፍትሃዊ አሰራር ያጋለጡት መረጃ የሚዲያችን እውነተኝነትና ለተበደለው ማህበረሰብ የምናደርገውን የዘውትር የመረጃ አብዮት ሀቅ ያስመሰከረ ነውና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አፋጣኝና ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ እናቀርባለን።