1000070595

ፕሮጀክቶችን አሳቦ ከፍተኛ ምዝበራ ተካሂዶበታል የተባለለት ጋሞ ልማት ማህበርና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ላይ ኦዲት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ትዕዛዝ በአርባምንጭ ከተማ ፕሮጀክቶችን ሰበብ አድረገው ከክልሉ ፋይናንስ ቢሮ እና ከጋሞ ልማት ማህበር ጋር በተያያዘ ተፈፅሟል የተባለው ምዝበራ በአስቸኳይ ኦዲት እንዲደረግ የክልሉ ምሁራን ጥያቄ አቅርበዋል።

ከክልሉ የተውጣጡ ምሁራን ለWT ሚዲያ በሰጡት አስተያየት የቀረበ ሲሆን፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት የክልሉ ሀብት በአብዛኛው ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ልማት እንደተዘዋወረና በልማት ስም ከፍተኛ ገንዘብ በጥቂት አመራሮችና ግለሰቦች እጅ መግባቱን ይገልጻሉ።

ምሁራኑ እንደሚሉት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተዳደር ለመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈል በሚቸገርበት ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ ላይ ከፍተኛ የመዋለ ንዋይ ፍሰት ታይቷል።

“አርባ ምንጭ እስክትለማ ሌላው ይድማ” በሚል መርህ የአርባ ምንጭ ከተማን ለማልማት ከፍተኛ የክልል በጀት ተመድቧል፣ ከተመደበው ገንዘብ ከግማሽ በላይ በአመራሮችና በጥቂት ግለሰቦች እጅ ገብቷል ብለዋል።

በተቃራኒው፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ፣ በዎላይታ እና በኮንሶ ዞኖች የልማት ፕሮጀክቶች ተከልክለዋል፣ የጨረታ ሂደቶች ተስተጓጉለዋል እንዲሁም ከሌሎች ብሔረሰቦች የተወጣጡ ኮንትራክተሮች ከስራ ታግደዋል ወይም ታስረዋል ሲሉ ለWT ሚዲያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ለዚህም ማስረጃ በሚል ባለፉት ሶስት ዓመታት በአርባ ምንጭ የተሰሩ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች በ5 ቢሊዮን ብር የተገነባው የአርባ ምንጭ ዓለም አቀፍ ስታድየም፣ የአርባ ምንጭ ገበታ ለትውልድ ኮንፍረንስ ሪዞርት ፕሮጀክት፣ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የከተማ ውስጥ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች፣ የጋሞ ልማት ማህበርን በክልል በጀት ማደራጀትና አቅሙን ማጎልበት፣ የጋሞ ቴሌቪዥን ጣቢያን ማቋቋም እንዲሁም ሌሎችም እንደ የከተማ ኮሪደር ልማትና የቱሪዝም ፕሮጀክቶች መሆኑ ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ ጊዜ በክልሉ ውስጥ ያሉ 11 ዞኖች ከልማት ተገለዋል ሲሉ ምሁራኑ አስረድተዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የክልሉን ሀብት በድጎማ ስም ለጋሞ ልማት ማህበር ሲያፈስ፣ ለሌሎች እንደ ጎፋ፣ ጌዴኦ እና ዎላይታ ያሉ የልማት ማህበራት ግን አንድም ብር ድጎማ እንዳላደረገ ጠቅሰዋል።

የጋሞ ልማት ማህበር እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ እንዲሁም ገቢዎች ቢሮ በገለልተኛ አካል ኦዲት እንዲደረጉ ጥያቄ ቀርቧል።

ይህም የገንዘብ አጠቃቀምን ግልፅነት ለማረጋገጥ እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን እንደሚያግዝ ተመላክቷል።

እንደምሁራኑ ገለፃ፦ የርዕሰ መስተዳድሩ ኢፍትሐዊ አሰራርና ሌሎች ዞኖች ከልማት እንዲገለሉ ከማድረግ ባሻገር በጋሞ ዞን በዛይሴ፣ ቁጫ፣ ካምባ፣ ጨንቻ እና ሌሎች ቦታዎች የህዝብ መሰረት ልማት ጥያቄ ተነፍገው በመንገድ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም የጤና ተቋማት እጦት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ጭምር እየተሰቃዩ እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ጥላሁን ከበደ አርባምንጭ ብቻ ትኩረት ያደረገበትን ሁኔታ ሲገልፁ፦ በያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ ከፍተኛ ጥቅም ትስስር በመፍጠር በግንባታ ሰበብ ለግሉ ገንዘብ ለመመዝበር እንዲመቸው እና አርባምንጭ ከተማ ውስጥ የረጅም ጊዜ የጥቅም ወዳጅ የሆኑ ግለሰቦች ፍላጎት ለማሳካት እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህንን የምዝበራ አላማ ለማሳካት ርዕሰ መስተዳድሩ የሚጠቀሙት ታማኝ ተላላኪ አመራሮችን በመሾም፣ ያለጨረታ በምስጢር ላደራጀው ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶችን እንዲሰሩ በማድረግ፣ የገቢዎች ቢሮን በመጠቀም እንዲሁም የህዝብ ተቋም የሆነውን ጋሞ ልማት ማህበር እንደ ጭምብል ተጠቅመው እንደሆነ ምሁራን አክለው አብራርተዋል።

በመጨረሻም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች፣ በተለይ ወጣቶች፣ ለፍትህ እና እኩል ልማት መብታቸው እንዲታገሉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የፌደራል መንግስት በክልሉ እየተስተዋለ ያለውን ኢፍትሃዊነት፣ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነት ህዝብን ከመንግሥት ወደመነጠል ደረጃ እየተሸጋገረ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ተጠይቋል።

ማሳሰቢያ፦ እንደዚህ አይነት ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ WT ሚዲያ በደስታ ተቀብሎ ያስተናግዳል። በተለይም ሚዲያችን በሀገሪቱ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት በሚዲያ ይፋ እናደርጋለን። እኛ የጭቁኖች አገልጋይ ነን!!