1000070615

የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) በቅርቡ በታዋቂው ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነ መስቀል ክንፈ ላይ የተፈጸመውን እስር በተመለከተ መንግስት ለህዝቡ አፋጣኝ እና ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

ንቅናቄው በዛሬው ዕለት ለWT ሚዲያ በላከው መግለጫ፣ ባለሀብቱ በምን ምክንያት እንደታሰሩ አሁንም ድረስ ግልጽ ያለመሆኑ እና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ ዝምታ መምረጣቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተተው አስታውቋል።

ዎብን ኢንጂነር ብርሃነ መስቀል በደቡብ ክልል እና በዎላይታ ማህበራዊ ልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ባለሀብት መሆናቸውን ገልጿል።

የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ የመንግስት ዝምታ የህዝብን እምነት የሚሸረሽር እና የህግ የበላይነት እየተመረጠ ነው የሚል ስሜት የሚፈጥር መሆኑን አብራርቷል።

ይህ ደግሞ ባለሀብቶች በዞኑ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ስጋት እንደሚፈጥር እና ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ላለበት አካባቢ ችግር ላይ ችግር መደራረብ መሆኑን አስረድቷል።

ንቅናቄው የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት የሚከተሉትን ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲያብራሩ ጠይቋል፦

ኢንጂነር ብርሃነመስቀል የታሰሩት በፍርድ ቤት ትእዛዝ ነው ወይስ በወንጀል ተጠርጥረው? የተጠረጠሩበት የወንጀል አይነት ምንድን ነው? ወንጀሉ የትና መቼ እንደተፈጸመ እና ምርመራው የተጀመረው በየትኛው አካል እንደሆነ (የደቡብ ክልል ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ወይም የጋሞ ዞን ፖሊስ)? እስሩ ህጋዊ ቢሆን እንኳን ከከተማ ወደ ከተማ ማንገላታት ለምን ተፈለገ ? የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት ይነፍጋል ወይ? በሚል ፓርቲው ጥያቄ አንስቷል።

በተጨማሪም ከቤተሰባቸው አካባቢ ርቀው ወደ ማቆያ ማእከል የተወሰዱት ለምን እንደሆነ በመጠየቅ የእስራቸው ምክንያት ከፋና ቴሌቪዥን የምርመራ ዘገባ “የማዕድን ሥር ቁማር” ጋር ግንኙነት አለው ወይ? መግለጫው ማንኛውም ግለሰብ ከህግ በላይ እንዳልሆነ ገልጾ፣ ህጉ በፍትሃዊነት፣ በግልጽነት እና የሰብአዊ መብት መከበር መተግበር አለበት ሲል አሳስቧል።

የመንግስት ዝምታ የእስሩ ምክንያት ከህግ አግባብ ውጭ ሊሆን ይችላል የሚል ፍራቻ እንደፈጠረ ገልጿል።

የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተል አስታውቋል፤ እንዲሁም በዎላይታ ህዝብ እና አጋሮቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል በዝምታ እንደማያልፍ አስታውቋል።