1000071610

በርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ‘አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ’ በሚል የተሰበሰበው ከስምንት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የት እንደገባ አለመታወቁ ተገለፀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አነሳሽነት በ2016 ዓ.ም. የተጀመረው “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” የተሰኘው ንቅናቄ አፈጻጸም ላይ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ እንደሚገኙ WT MEDIA ለመታዘብ ችሏል።

የክልሉ መንግስት መጀመሪያ ላይ ንቅናቄው ስኬታማ መሆኑን ቢገልጽም፣ የተማሪዎች የመጽሐፍ እጥረት ችግር አሁንም እንደቀጠለ እንደሆነ ከክልሉ ከተለያዩ አከባቢዎች ለ WT MEDIA የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም የተነሳ በንቅናቄው የተሰበሰበው ከፍተኛ ገንዘብ የት ገባ የሚለው ጥያቄ የበርካቶች አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

በወቅቱ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን እንደገለጹት፣ ለንቅናቄው ማስጀመሪያ ይሆን ዘንድ የክልሉ መንግስት 300 ሚሊዮን ብር መድቦ ነበር።

በተጨማሪም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመለገስ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት ድጋፍ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መገመቱን የክልሉ መንግስት አስታውቆ እንደነበር መረጃዎችና ሰነዶች ይጠቁማሉ።

ሆኖም፣ አሁን ላይ ተማሪዎች አሁንም በመማሪያ መጽሐፍ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸው እየተነገረ ይገኛል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አንድ መጽሐፍ ከመጋራት አልፎ የመማሪያ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ የሌላቸው እንደሆኑ ተገልጿል።

ይህ ሁኔታ በንቅናቄው ተሰብስቦ የነበረው በጠቅላላው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ገንዘብ በምን መልኩ እና በምን ላይ እንደዋለ ግልጽነት እንዲሰጥ የህዝብ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር፣ በክልሉ ውስጥ ለተለያዩ ዓላማዎች በንቅናቄ መልክ ተሰብስቦ ግልጽነት የጎደለው ገንዘብ ላይ ማጣራት እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።

ለምሳሌ ያህል፣ ለክልሉ ምስረታ ተብሎ የተሰበሰበው 2 ቢሊዮን ብር እና ለጎፋ መሬት ናዳ አደጋ ተፈናቃዮች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በሌሎች ንቅናቄ ተሰብስቦ የት እንደገባ የማይታወቁ ገንዘቦች ምርመራ እንዲደረግለት ጥያቄ ቀርቧል።

የህዝብን ገንዘብ ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተዳደር የመልካም አስተዳደር ዋነኛ መገለጫ ነው።

በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በተነሱት ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ምርመራ በማድረግ የገንዘቡን አጠቃቀም በተመለከተ ለህዝብ ግልጽነት ሊሰጡ ይገባል ሲሉ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች እያሳሰቡ ይገኛሉ።