የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ መስራች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ አንዱዓለም ታደሰ ቦልጠና፣ በስዊድን የደህንነት መስሪያ ቤት በግለሰባዊ ደህንነታቸው ላይ ስጋት እንዳለ መወሰኑን ገልጸዋል።
ይህንን ያሳወቁት ዛሬ ባወጡትና ለ WT Media በላኩት የፕሬስ መግለጫ ነው።
በመግለጫቸው፣ አቶ አንዱዓለም ላለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ የደህንነት ጥቃቶችና እንግልቶች እንደደረሱባቸው አመልክተዋል።
ከእነዚህም መካከል የምግብ መመረዝ፣ ታፍኖ መወሰድ፣ ኢሰብአዊ የሆነ አያያዝ፣ አካላዊና ስነ-አእምሮአዊ ጉዳቶች እንዲሁም ስም ማጥፋት፣ ገንዘብና ንብረት መነጠቅን ጨምሮ በርካታ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው አስረድተዋል።
እነዚህ ጥቃቶች ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በመግለጫው ላይ አብራርተዋል።

አቶ አንዱዓለም፣ የስዊድን መንግስት በደህንነታቸው ላይ ስጋት መኖሩን ማመኑ ለመፍትሄው የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ አጋጣሚም የስዊድን የደህንነት መስሪያ ቤትን ለገለልተኝነቱና ለሙያዊነቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በመግለጫቸው ላይ፣ ከእርሳቸው እና ከቤተሰባቸው ደህንነት ጋር በተያያዙ ተግባራት ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ይህንን ጥሰት የሚፈጽም ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን በስዊድን የፀረ-ስለላ ህግ መሰረት ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቀዋል።
አቶ አንዱዓለም፣ የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት እና በስቶክሆልም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለደረሰባቸው ጥቃት ተጠያቂ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የህግ የበላይነት እንደሚሰፍን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመግለጫቸው ማጠቃለያ ላይ “እውነት ትዘገያለች እንጂ ተደብቃ አትቀርም” በማለት መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።
የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ መስራች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ አንዱዓለም ታደሰ በኢትዮጵያ ፓለቲካ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ፣ ትችት እንዲሁም የመፍትሔ ሀሳቦችን በመስጠት ይታወቃሉ።