1000072011

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለተማሪ መጽሐፍ ግዢ በሚል በንቅናቄ የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደገባ በሚዲያ ከተጠየቀ በኃላ ከክልሉ የተሰጠው ማስተባበያ ተጨማሪ ጥርጣሬ መፍጠሩ ተገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከዓመት በፊት በርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ አነሳሽነት የተጀመረው “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” የተሰኘው ንቅናቄ ስለተሰበሰው አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ጉዳይ ላይ ጥያቄዎች WT Media በመረጃ የተደገፈ ዘገባ መስራቱን ተከትሎ፣ የክልሉ መንግስት ለክሱ ምላሽ ሰጥቷል።

ክልሉ በዛሬው ዕለት ለማስተባበል ባወጣው መግልጫ፣ ትምህርት ቢሮው በ227 ሚሊዮን ብር የመማሪያ መጻሕፍት ታትመው እየተሰራጩ መሆኑን ገልጿል።

ይሁን እንጂ የህዝቡ ጥያቄዎችና ስጋቶች አሁንም እንዳልተመለሱና ይበልጥ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረጉ እየተነገረ ይገኛል።

ከሶስት ቀናት በፊት WT Media ባወጣው ዘገባ፣ በ2016 ዓ.ም. በተጀመረው ንቅናቄ ለተማሪዎች መጽሐፍ ለመግዛት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ መገመቱን ጠቁሟል።

ከዚህ ውስጥ 300 ሚሊዮን ብር የመንግስት ድጋፍ ሲሆን፣ ቀሪው 500 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከመንግስት ሠራተኞች እና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበ እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል።

ዘገባው ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተሰብስቦ እያለ፣ አብዛኛው የክልሉ ተማሪዎች ግን አሁንም በመማሪያ መጽሐፍ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን እና በገንዘቡ አጠቃቀም ላይ ግልጽነት እንደሌለበት መረጃ አቅርቧል።

WT Media ዘገባውን ካወጣ ከሶስት ቀናት በኋላ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ፀሐይ ወራሳ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጋር በመሆን በዛሬው ዕለት ለተነሳው ክስ ማስተባበያ ሰጥተዋል።

ኃላፊዋ በ227 ሚሊዮን ብር የመማሪያ መጻሕፍት መታተማቸውን አረጋግጠዋል።

ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 127 ሚሊዮን ብር ከ”አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው 100 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከክልሉ መንግስት በጀት የተሸፈነ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ1 ሚሊዮን 580 ሺህ በላይ መጻሕፍት መታተማቸውን እና የመጽሐፍ ተማሪ ጥምርታው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል 1ለ3 መድረሱን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የክልሉ መንግስት የሰጠው ምላሽ በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ጥያቄዎችን አሁንም እያስነሳ ይገኛል።

የገንዘቡ አለመጣጣም፦ የትምህርት ቢሮው ከመጽሐፍ ንቅናቄው የተገኘው ገንዘብ 127 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ቢልም፣ በመጀመሪያው ዙር ንቅናቄው ወቅት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቀሪው ከ673 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ገንዘብ የት እንደገባ የሚገልጽ ግልጽ መረጃ አልተሰጠም። ይህ ትልቅ የገንዘብ ክፍተት ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

ግልጽነትና ኦዲት፦ እንደ ዘገባው መረጃ ከሆነ፣ ንቅናቄው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተሰበሰበው ገንዘብ በገለልተኛ አካል ኦዲት ተደርጎ አያውቅም። የህዝብ ገንዘብ በግለሰቦች እጅ እየገባ እንደሆነ እና ያለ አግባብ ለሌላ ዓላማ እየዋለ እንደሆነ ስጋቶች እየተነሱ ነው።

የተሰበሰበ ገንዘብ ዓላማ፦ በክልሉ ውስጥ ለተለያዩ ዓላማዎች፣ ለምሳሌ ለክልሉ ምስረታ እና ለጎፋ የመሬት ናዳ አደጋ፣ በንቅናቄ መልክ ከፍተኛ ገንዘብ ቢሰበሰብም የት እንደዋሉ ግልጽ አለመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል።

በአጠቃላይ፣ የክልሉ መንግስት የሰጠው ምላሽ በገንዘብ አጠቃቀም ላይ ያለውን ግልጽነት ሙሉ በሙሉ አላስቀመጠም።

የህዝብን ገንዘብ በግልጽ ማስተዳደር የመልካም አስተዳደር ዋነኛ መገለጫ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት ቀሪው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በምን መልኩ እና በምን ላይ እንደዋለ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ እና አስፈላጊ ከሆነም ገለልተኛ ኦዲት እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።

ለምሳሌ ያህል፣ ለክልሉ ምስረታ ተብሎ የተሰበሰበው 2 ቢሊዮን ብር እና ለጎፋ መሬት ናዳ አደጋ ተፈናቃዮች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በሌሎች ንቅናቄ ተሰብስቦ የት እንደገባ የማይታወቁ ገንዘቦች ምርመራ እንዲደረግለት ጥያቄ ቀርቧል።