የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመጣስ ባሻገር ባላለቀ ፍርድቤት ጉዳይ ተበዳይ ባለሀብቱን በህገወጥ መንገድ አስሮ እያሰቃየ መሆኑ በክልሉ የሚስተዋለውን ስርዓት አልበኝነት በግልጽ የገለጠ እንደሆነ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እግዱን ማክበር እና ምስከበር፣ መፈፀም ሲገባው የፍርድ ቤቱን የእግድ ትእዛዝ ያልተከበረበት ምክንያት በአካል ቀርበዉ እንዲያስረዱ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ከመጣስ ባሻገር ተበዳይ ባለሀብቱን በህገወጥ መንገድ ማሳሰሩ አነጋጋሪ ሆኖ መቀጠሉ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮምሽን ም/ኮምሽነር ጉራማይሌ የተባለ የክልሉ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ቀጥታ ከኮምሽኑ እውቅና ውጪ ከርዕሰ መስተዳድሩ የሚሰጠውን ተልዕኮ ብቻ በመውሰድ በክልሉ የወንጀል ተባባሪ መሆኑ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተገልጿል።
ኮምሽኑ ሁሉንም የመንግስት መዋቅርን በመጠቀም የራሱን ቡድን ፍላጎት ለማሳካት ህገወጥ መንገድ እየተጠቀሙ የሚገኙትን የርዕሰ መስተዳድሩን ህገወጥ ትዕዛዝ ለመፈጸም ተቋማዊና ሙያዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአከባቢው ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ እያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።
ለአብነትም የማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነ መስቀል በደሉን ወደ ፍርድ ቤት ከመዉሰዱ ባሻገር የፓርቲ ሚዲያ የሆነዉ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መጥቶ በክልሉ ዉሃና ማዕድን ቢሮ ዉስጥ የሚፈፀመዉን ብልሽትና ሌብነት እንዲያጋልጥ አድርጓል የሚል ቂም ይዘው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የክልሉን ፖሊስ ኮምሽን (ም/ኮምሽነር ጉራማይሌ) እና ሌሎች የፍትህ ተቋማትን በመጠቀም ጉዳዩ ገና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ጉዳይ ክርክር ላይ እያለ ህግን ጥሰው ባለሀብቱን አስሮ እያሰቃየ ይገኛል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ 6ኛ ንግድ ይግባኝ ችሎት መዝገብ ቁጥር 337812 በሰጠው ትዕዛዝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ እግዱን ማክበር እና ምስከበር፣ መፈፀም ሲገባቸዉ የፍርድ ቤቱን የእግድ ትእዛዝ የተጣለበት ምክንያት በአካል ቀርበዉ በቀን 04/02/2018 ዓ.ም እንዲያስረዱ አዝዟል።
ለመልስ ሰጪ ፍርድ ቤቱ ደግሞ ችሎቱ የሰጠዉ የእግድ ትእዛዝ መሰረት በስሩ ካሉት የጋሞ ዞን አስተዳደር፣ የቦረዳ ወረዳ አስተዳደር ጋር በመሆን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር፣ እግዱ እንዲፈፀም በጥብቅ ታዟል ሲል WT Media የተመለከተው ከፍርድቤት የተሰጠው ሰነድ መረጃ ያስረዳል።

በተጨማሪም ፍርድቤቱ፦ “የፌደራል ፖሊስ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ፣ የጋሞ ዞን ፖሊስ፣ የቦረዳ ወረዳ ፖሊስ በዚህ ፍርድ ቤቱ በቀን 06/08/2017 ዓ/ም እና በቀን 13/08/2017 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት የሰጠዉ የእግድ ትእዛዝ እንዲደርሳቸዉ፣ እግዱ እንዲከበር እና እንዳይጣስ ተገቢዉን ክትትልና እንዲፈፀም እንዲያደርጉ በጥብቅ ታዟል” የሚል ግልጽ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮምሽን እና የክልሉ ፍትህ ተቋማት የርዕሰ መስተዳድሩን ህገወጥ ትዕዛዝ ለመፈጸም ተቋማዊና ሙያዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአከባቢው ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት እንዳይጥል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ተበዳይ ወጣት ባለሀብት ብርሀነመስቀል እንዲታሰር በማድረግ በክስ ሂደት ላይ ባለው ቦታ ገብተው በርዕሰ መስተዳድሩ ትዕዛዝ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ከአምስት ባላይ ድርጅቶች እየሰሩ እንደሚገኙ የዕግድ ትዕዛዝ ለመስጠት የመጡት የፈደራል ፖሊስ በትናንትናው ዕለት ከቦታው አረጋግጠዋል።
ከ32 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ያቀፈዉን ክልል ይመሩ ዘንድ ቢሾሙም ሌላዉን አካባቢ ማየት ተስኗቸዋል ተብለዉ እና ስልጣናቸዉን ተገን በማድረግ ሌብነት ዉስጥ በመዘፈቃቸዉ በተጨባጭ የሚተቹት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ከከሰል ድንጋይ ማዕድን ጋር በተገናኘ የተፈፀመበትን በደል በፍርድ ቤት እየሞገተ የሚገኘዉን ወጣቱን የማራ ማይነርስ ባለቤትን አቶ ብርሃነ መስቀልን የባለሀብቱን ሰብዓዊ መብት በጣሰ መንገድ ከከተማ ወደ ከተማ እያዞሩ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል (አድማ ብተና) ካምፕ በማሰርና ህክምና ጭምር እንዳያገኝ በማድረግ ወደ ጉዳዩ ወዳለበት ወደ ጋሞ ሳይሆን ወደ ሳውላ ከተማ ማረሚያ እንዲጣል መደረጉ ተነግሯል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአከባቢው ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያላቸውን የንግዱ ማህበረሰበንና ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ በግልጽ የከተማዋን ዕድገት ወደኋላ የመመለስ እቅድ የተሰራ እንዲሁም በህጋዊ መንገድ የተለያዩ ግዙፍ ፋብሪካ ጀምሮ እንቨስትመንት ለመስራት መሬት ተረክበው በአከባቢው ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንቅስቃሴ የጀመሩ ባለሀብቶች ስራ እንዲቆም መደረጉን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የሚደርሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።