1000072183

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የፖለቲካ ብልሽቱን ለመቅረፍ የሀገር ሽማግሌዎችን ያቀፈ መማክርት ለማቋቋም መጀመሩ ተገለፀ።

በዛሬው ዕለት የተጀመረውን ይህንን እንቅስቃሴ ተከትሎ ግን በርካቶች የመማክርቱ ህጋዊነት፣ የአመራር ምርጫ እና የሂደቱ ግልጽነት ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ።

ለሚመሰረተው መማክርት መሪ አድርጎ አክቲቪስትና በማህበራዊ ሚዲያ በጥላቻ ህዝብን ከህዝብ በማለያየት እንቅስቃሴ የሚታወቀው አቶ ሳድቃ ስሜ የሚመሰረተውን መማክርት ህግና ደምብ ለማውጣት መሪ ተደርጎ መመረጡ አነጋጋሪ ሆኗል።

“የጥላቻ አባት” እና “የሴራ ጠንሳሽ” ተብሎ የሚጠራው አቶ ሳድቃ፣ “ለእኔ ከደቡብ ይልቅ ጎንደር ይቀርበኛል” በሚል አባባሉ ይታወቃል።

ይህ ምርጫ የሚቋቋመው ምክር ቤት እምነትና ህዝባዊ ተቀባይነት ያሳጣዋል የሚል ስጋት ተንጸባርቋል።

የመማክርቱ ምስረታ ህጋዊ መሰረትም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

የዜናው ምንጭ የሆኑ የህግ ባለሙያዎች፣ ተቋሙ በአዋጅ ወይስ በርዕሰ መስተዳድሩ ትዕዛዝ እንደተቋቋመ ግልጽነት እንደሌለው ገልጸዋል።

እንደ ሲቪክ ማህበር መመዝገብ የሚገባው አካል በክልል መንግስት ጣልቃ ገብነት መቋቋሙ ህጋዊነቱን አጠያያቂ እንደሚያደርገውም ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የመማክርት ምክር ቤቱ አባልነት ለወንድ ሽማግሌዎች ብቻ የተገደበ ነው ወይስ የሴት ሽማግሌዎችን ሚና ያካትታል የሚለውም አልተብራራም።

WT Media እንደታዘበዉ በርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ የሚመራው ይህ እንቅስቃሴ፣ የህዝብ ተቀባይነት በሌላቸው ሰዎች የሚመራ ነው ተብሎ ተወቅሷል።

አቶ ጥላሁን በተለያዩ አካላት የሙስና፣ ብልሹ አሰራር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በመፈጸም ሲከሰሱ እንደነበር የዜናው ምንጭ አትቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለሽማግሌዎቹ ባደረጉት ንግግር፣ “አባቶች የውሸት ትርክት በመፍጠር ማህበራዊ ሚዲያን ለእኩይ አላማ ከሚጠቀሙ አደናጋሪዎች ህዝቡ እንዲጠበቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይገባችኃል” ብለዋል።

ይህ አባባል የማህበራዊ ሚዲያ ጥቆማዎችን ከመፍራት የመጣ እንጂ ለዘላቂ ችግር መፍታት ያለመ አይደለም የሚል ትችት ቀርቦበታል።

በአጠቃላይ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሽማግሌዎች ምክር ቤት፣ ቀደም ሲል የክልሉ አስፈጻሚ አካላት እና ፍርድ ቤቶች ማሳካት ያልቻሉትን ሰላምና ፍትህ ያመጣል ተብሎ እንደማይታመን የተገለፀ ሲሆን ይልቁንም በፖለቲከኞች ፍላጎት ብቻ የሚመራ በመሆኑ ከወዲሁ እምነት የሚጣልበት እንደማይሆን ተዘግቧል።