በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በሚገኘው የዛይሴ ብሔረሰብ ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉን የWT Media ምንጮች አረጋግጧል።
በአከባቢው ከወር በፊት በደረሰ የኃይል እርምጃ በርካታ ሰዎች ሲገደሉና ቤቶች በእሳት ሲጋዩ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ አዲስ የጥቃት ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆናቸው ተሰምቷል።
በዛሬው ዕለት ለ WT Media በደረሰው ዘገባ መሠረት፣ የዛይሴ ፋንጎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሽብሩ ሸላ ሙዝ የተባሉ ግለሰብ፣ ባለ 2 ሄክታር የሙዝ እርሻቸው ትናንት ምሽት (ጳጉሜ 4) በገንዘብ ግብረ አበር በተደራጀ ኃይል መውደሙን ከስፍራው አረጋግጧል።

አቶ ሽብሩ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በፍትህና ፀጥታ ኃላፊነት የሾሙትን አቶ ጎቾራ ሻንቆ እና እህታቸው ኢንቨስተር አልማዝ ሻንቆን ነው።
አቶ ሽብሩ ከዚህ ቀደምም በፖለቲካ እና ልዩ ወረዳ የመዋቅር ጥያቄ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ከቤተሰባቸው ተለይተው በስደት ላይ መኖራቸውን ለ WT Media ገልጸው፣ ፍትህ ከፌዴራል መንግስት እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የዘይሴ ሻንካ አካባቢ ነዋሪዎች ዛሬ ጠዋት የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስ እና የክልሉ ፀጥታ አካላት በአርሶ አደሮች ማሳ በመግባት ጎተራዎችንና ማማዎችን በእሳት ማውደማቸውን ገልጸዋል።

ይህ ድርጊት አርሶ አደሮች የእርሻ ስራ እንዳይሰሩ መከልከላቸውንና ህዝቡን ሰው ሰራሽ ረሃብ ውስጥ ለመጣል ያለመ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ይህ ሁኔታ የዛይሴ ብሔረሰብ ላይ ከወራት በፊት ሲደርስ የነበረውን ጥቃት ተከትሎ የመጣ ነው። ከአንድ ወር በፊት WT Media የዘገበው ዘገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አብርሃም አሞሼ እንደገለጹት፣ ከግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በጋሞ ዞን አመራሮች አስተባባሪነት በተፈጸመ ጥቃት 12 ሰዎች ሲገደሉ 98 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
አቶ አብርሃም በወቅቱ ለWT Media እንደተናገሩት፣ ሕገወጥ ታጣቂዎች (ልዩ ኃይል/አድማ በታኝ) እና የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊሶች ንብረት እየዘረፉ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጭምር የሰብአዊ መብት እየጣሱ፣ ቤትና ንብረት በእሳት እያወደሙ ነው ብሏል።

አቶ አብርሃም ይህን የኃይል እርምጃ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጋሞ ዞን አመራሮች ሽፋን እየሰጡት ነው ሲሉ በግልጽ አስታውቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የዛይሴ ብሔረሰብ የራሱን የአስተዳደር መዋቅር ለማግኘት ካቀረበው ሕጋዊ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን ጥቃት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአካባቢያቸው መሰደዳቸው እና ንጹሃን ዜጎች ለረሃብና ፍርሃት መጋለጣቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የአካባቢው ነዋሪዎች እና የብሔረሰቡ ተወካዮች፣ እየደረሰ ያለው የኃይል እርምጃ “ግልጽ የዘር ማጥፋት” ወንጀል መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት እና የፌዴራል መንግሥት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ WT MEDIA በደስታ ተቀብሎ ያስተናግዳል። በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media
#Ethiopia #southethiopia