received_1345903443760829

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከርዕሰ መስተዳድር ብቻ ምስጥራዊ ተልዕኮ በመውሰድ ባለሀብቶችንና ሌሎች ግለሰቦችን ለማስፈራራት፣ ለማሰር፣ ገንዘብ እንዲቀበልና ሰብዓዊ መብት ለመጣስ በህግ ያልተፃፈ ፈቃድ የተሰጠውን ምክትል ኮምሽነር|ን ያውቃሉ ?

አንድ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮምሽን ላይ ከፍተኛ መኮንን የሆነው ለህዝብና ለመንግሥት ጥቅም ሲባል ወደ አደባባይ መውጣት ያለበት በሚል በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተልዕኮ ሰጭነት አሳዛኝ ህገወጥ ድርጊት እየፈጸመ ስለሚገኘው ምክትል ኮምሽነር ጉራማይሌ ጉርኦ ስለተባለው ግለሰብ በተመለከተ ለWT Media መረጃና ማስረጃ አስደግፎ አድርሷል።

“‎ምክትል ኮምሽነር ጉራማይሌ ጉርኦ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ዘርፍ ኋላፊ ሲሆን የአቶ ጥላሁን ከበደ ቀኝ እጅ ነው። በእሱ ምክንያት የታሰረና ከተቋሙ የለቀቁ ወላይታ ሰው ቁጥር ስፍር የለውም። ሰውየው ከተቋሙ መሪ ከሆነው ኮሚሽነር ይልቅ ቀጥታ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተልዕኮ ይቀበላል” በሚል ከፍተኛ መኮንኑ አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

አክለውም “‎ግለሰቡ አደገኛ ክራይ ሰብሳቢና የስነምግባር ጉድለት ያለበት ነው። ባለፈው ባለሀብቱን (ብራሀነመስቀል) ከአዲስአበባ በመያዝ እስከ ዲላ ድረስ በመንገድ አሰቃይቶ ጎፋ ያደረሰው እሱ ነው። በዎላይታ ‎ሰዶ ከተማ አመራሮችንና የዎላይታ ዞን አመራር እንደፈለገ ያደርጋቸዋል። ማንንም አስራለሁ ብሎ ማስፈራራት ብቻ ሳይበቃው ይህንን የውሸት ምርመራ ለመምራት የራሱን ሰው አዘጋጅተው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል” ብሏል።

እንደ ከፍተኛ መኮንኑ ገለፃ “በአጠቃላይ ምክትል ኮምሽነር ጉራማይሌ ጉርኦ፣ በዎላይታ ውስጥ ባለሀብትን ምርመራ በአንተ ላይ አስጀምሪያለሁ በማለት እያስፈራራ ገንዘብ እየሰበሰበ መሆኑ ሳይበቃው በሚያሳዝን ሁኔታ ሆቴል ላይ ሴትና መጠጥ ካላዘጋጁ ነገ ጥዋት ቢሮ ና እያለ በመጥራት ጭምር እንደሚያስፈራራ እንደፈለገ እንደሚያስርም አብራርተዋል።

ምክትል ኮምሽነር ጉራማይሌ ጉርኦ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ዘርፍ ኋላፊ

“ስለዚህ ይሄንን የፈሩ ባለሀብቶች በሶዶና በበዲቲ ከተማ ህፃናት ሴቶችን ገንዘብ በመስጠት ለዚህ ሰውዬውን አምጥተው ከእሱ ጋር ያሳድራሉ። በጣም የምያሳዝነው ይህንን ሴት እህቶቻችንን ለተለያየ አደጋ እያጋለጠ የሚገኘውን ህገ ወጥ ስራ ስማቸው ለጊዜው አልናገርም እንጂ እነሱ ይመራሉ” በሚል በክልሉ ፖሊስ ኮምሽን ላይ ከፍተኛ መኮንን የሆነው ለህዝብና ለመንግሥት ጥቅም ሲባል በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተልዕኮ ሰጭነት አሳዛኝ ህገወጥ ድርጊት እየፈጸመ ስለሚገኘው ምክትል ኮምሽነር ጉራማይሌ አስረድተዋል።

ለማሳያነት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በመረጃ አስደግፈን እንደዘገብነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተልዕኮ ሰጭነት፣ የባለሀብቱ ከሳሽ የሆነው የክልሉ ውሃ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አዳኝ አማካይነት፣ ከህግ አግባብ ውጪ የዎላይታውን ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብራሀነመስቀል ክንፈን፣ ከተቋም እውቅና ዉጪ የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ጉራማይሌ ጉርኣ (የጎፋ ተወላጅ) አዲስአበባ ድረስ በመላክ እና ህዝብና መንግስትን ለመጠበቅ የቆመን የፖሊስ ሰራዊትና ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም፣ ወጣቱን ያልተፈጸመ ወንጀል ፈጽሟል የሚል ሽፋን በመስጠት በጎፋ ማረሚያ ግዞት አስቀምጠውታል።

ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብራሀነመስቀል ክንፈ

በ “ማዕድን ስር ቁማር” በተሰኘው የፋና ምርመራ ዘገባ ያጋለጠውን የሙስና ወንጀል እና በክልሉ ያለውን ብልሹ አሰራር አጋልጠሃል በሚል የቅም በቀል በመነሳት የከሳሽን ወንድም ዳኛ አብራሃም አዳኝ ጭምር ተጠቅሞ የሀሰት ክስ በመመስረት አቶ አክሊሉ አዳኝ በበላይነት በሚመራው ጎፋ ዞን ላይ ወጣቱን ባለሀብት በግፍ አስረውና ህገመንግስታዊ የዋስትና መብቱን ጭምር በመከልከል የወጣት ባለሀብቱ የሆነውና በፍርድቤት እግድ ላይ የሚገኘውን የቦሮዳ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ቦታ በጥቅም ተጋሪዎቻቸው በህገወጥ መንገድ በመስጠት ዝርፊያው እየፈጸሙ እንደሆነም በደረሰን መረጃ ላይ ተገልጿል።

ከቀናት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የክልሉን ብልሹ አሰራሮችና መብቱን በፍርድቤት ለማስከበር ባደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት በግፍ ታስሮ በሚገኘው የማራ ማይነርስ ባለቤት፣ ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ በታሰረበት በሳውላ ማረሚያ ተቋም የተደረገው የተጠና የግድያ ሙከራ በተቋሙ ጠንካራ ስራና ክትትል ሊከሽፍ መቻሉን WT Media ያገኘው መረጃ አረጋግጠን መዘገባችን ይታወሳል።

በዚሁም ከክልሉ ኮምሽን እውቅና ዉጪ የተቋሙ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ጉራማይሌ ጉርኣ (የጎፋ ተወላጅ) አስተባባሪነት በተቀናጀ ሁኔታ ግድያ ለመፈፀም ሌላ ቦታ እሰረኛ የሆነውን ታራሚ የዚህን የእኩይ ቡድኑ ተልእኮ ተሰጥቶት ከታሰረበት ዲላ ማረሚያ ወደ ሳውላ ማረሚያ እንዲዛወር በማድረግ በዚህ በሳውላ ማረሚያ የሚገኘውን ወጣቱን ባለሀብት ብራሀነመስቀል ላይ ግድያ እንዲፈጽም የተላከ ቢሆንም፣ የሳውላ ማረሚያ ተቋም መረጃው በመድረሱ ወደ ዲላ ማረሚያ እንዲመለስ መደረጉን ከስፍራው ለ WT Media አፈትልኮ የደረሰው መረጃው ይጠቁማል።

ከዚህ በፊት ወጣት ባለሀብቱ ወደ ጎፋ በተወሰደበት ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊት አቶ ጥላሁን ከበደ በግፍ ያሳሰረውን የማራ ማይነርስ ባለቤት አቶ ብርሃነመስቀልን እንዲያሰቃይ የሰጠውን ትዕዛዝ “አልቀበልም፣ እንደማንኛውም እስረኛ የሰብዓዊ መብት ክብሩን እጠብቃለሁ” በማለቱ ጥላሁን ከበደ በቀን 22/12/2017 ዓ.ም በሳውላ ከተማ በመገኘት በሰጠው ቀጥታ ትዕዛዝ ተወዳጁ እና ታታሪው ወጣት የፖሊስ አዛዥ ደሳለኝ ጩቱሎ በግፍ ከስራ መታገዱን እና መታሰሩን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ በኩል “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በባለሃብቱ ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ ላይ የመሰረቱት ክስ ፍሬ ነገር ሲጨመቅ ባለሃብቱን ለማጉላላትና በማረሚያ አክርሞ ለመበቀል ካልሆነ በቀር ጭብጡ ውሃ የሚያነሳ አይደለም” ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በቀዳሚነት የሙስና ወንጀል ዋና ፈጻሚ ሳይኖር ከዋና ፈጻሚዎች ጋር በድርጊት በመተባበር በሚል የቀረበው ክስ የት ከማን ጋር መቼ እና እንዴት የሚሉ መሰረታዊ የድርጊት ወይም ክዋኔ ዑደቶችንና ሂደቶችን የማያመላክት እጭቅ ፍረጃ እንጂ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ቀርቦበት የተደራጀ ክስ አይደለም ብለዋል።

ሲቀጥል በፍትሐብሄር የወንጀል ዘውግ ላይ የሚወድቀው “ይህን ያህል ኪሳራ ደርሶብኛል” የሚለው ክስም ቢሆን ግለሰቡ ከክልሉ ጋር ያለውን አለመግባባት በውይይትም ሆነ በድርድር ለመፍታት የሚያስችል ቀናነት በማጣቱና በደም እና በአከባቢያዊነት ማሰብና መመዘን በመጀመሩ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወስዷል ሲሉ ባለሙያዎቹ አስረድተዋል።

ጉዳዩ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እየታየ እያለ የፍርድ ቤት እግድ ጥሰው “የእኛ” ለሚሏቸውና በጥቅም ለተሳሰሯቸው ባለሃብት ግለሰቦች እንዲሁም የክልሉ ቱባ አመራሮች በስውር ባደራጇቸው ማህበራት ሊቀራመቱ የግለሰቡን ይዞታ መሸንሸን ተገቢነት የለለው ህገወጥ ተግባር ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በተጨማሪም “ክልሉ ላይ ፖሊስ የጥቂት ባለስልጣን ነን ባዮች መቀለጃ ወደመሆን እየተቃረበ መጥቷል። እከሌን እሰር ሲባል የሚያስር ፍታ ሲባል የሚፈታ ተላላኪ ሆኗል። ከሙያቸው ይልቅ ሆዳቸውን የሚያስቀድሙ አዛዥ ነን ባይ ደላሎች መዋቅሩን ሞልተውታል። እናዝናለን። ፍርድ ቤቶች በአንፃራዊነት ተቋማዊ ነጻነታቸውን ድንበር አያስደፍሩም። ጥቂቶች ቢያሸረግዱም አብዛኛዎቹ በህሊናቸው ይዳኛሉ። ህዝብም ይጠብቃችኋል። ፍትህ ሲሰፍን ሀገር ነውና የሚረካው” በሚል የህግ ባለሙያዎች ሀሳባቸውን አክለዋል።

የህግ ባለሙያዎችም በባለሀብቱ ላይ የተመሰረተው ክስ ህገወጥ እና የፖለቲካ የበቀል እርምጃ መሆኑን እንዲሁም ህጋዊ ስልጣን በሌላቸው አካላት የተጀመረ ህገወጥ ክስ እንደሆነ ገልፀው ይህ ክስተት በክልሉ የህግ እና የፍትህ ስርዓት ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።