የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች በዋስትና እንዲለቀቁ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፀና
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ከሁለት ሳምንት በላይ በእስር ላይ የቆዩትን የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች በ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል።
የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ አርታኢ ትዕግስት ዘሪሁን እና ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው በዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋዜጠኞቹ ከእስር ቢለቀቁ ማስረጃ ሊያጠፉ ይችላሉ በሚል ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደርጓል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ከእስር ከተለቀቁ ማስረጃ ያጠፋሉ የሚለውን የፖሊስ ማመልከቻ ባለመቀበል፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ዛሬ በዋለው ችሎት መወሰኑን ሸገር ኤፍ ኤም አስታውቋል።
የክስተቱ ዳራ
ጋዜጠኞቹ ለእስር የተዳረጉት ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም ሲሆን፣ ይህም ነሐሴ 24 ቀን 2017 በሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ፣ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ያቀረቡ የጤና ባለሙያዎች ከጤና ሚኒስቴር የተሰጣቸውን መፍትሄ ሰርኩላር እንዴት እንደሚመለከቱት የሚጠይቅ ዜና ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው። የዜናና ፕሮግራም ኃላፊው እሸቴ አሰፋ ከጋዜጠኛ ምንታምር ፀጋው ጋር በዕለቱ ከቢሮ ከተወሰዱ በኋላ ቃላቸውን ሰጥተው የተለቀቁ መሆኑ ተመላክቷል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዜናውን “የሽብር ፈጠራ ወንጀል ነው” በማለት ክስ መስርቷል። ሬዲዮ ጣቢያው እንደገለጸው፤ ፖሊስ ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው “በተለያዩ የሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ችግር እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሀሰተኛ መረጃና ወሬዎችን በማሰራጨት፣ በከተሞች አመፅ በመቀስቀስ፣ መንግስትና ሕዝብ እርስ በርስ እንዲጋጩ በማድረግ፣ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን በመሳደብ እና በማስፈራራት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በመንቀሳቀስ አመፅ ቀስቃሽ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን በመልቀቅ የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ” በቁጥጥር ስር ማዋሉን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ የዋስ መብታቸውን የሚያስከለክል ነገር ባለመኖሩ እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ መስከረም 7/2018 ዓ.ም ውሳኔ ሰጥቷል።

ጣቢያው በዚያው ዕለት የዋስትና ፎርማሊቲ ተሟልቶ ዳኛው የፈረሙበት ትዕዛዝ ለወንጀል ምርመራ ቢሮው ቢደርስም፣ እስረኞቹ አለመለቀቃቸውን አስታውቋል። ከዚያም መስከረም 8 ፖሊስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ማለቱና ለመስከረም 12/2018 ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙ ተገልጿል።
መስከረም 12 ቀን ፖሊስ፣ ከመስከረም 7 ጀምሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ዘገባው ከድረ ገጹ ላይ መነሳቱ ሌሎችንም ማስረጃዎች ሊያጠፉ እንደሚችሉ ስለሚያሳይ፣ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሻርለት ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት አመልክቷል። የጋዜጠኞቹ ጠበቃ ደግሞ ደንበኞቹ የታሰሩት መስከረም 7 ሳይሆን ነሐሴ 28 መሆኑን፣ መረጃው ከድረ ገጹ ላይ የወረደው በተቆጣጣሪው ባለስልጣን አስተያየት መሆኑንና ሙሉ ዜናው በፖሊስ እጅ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ነገሩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 14 ቀን 2018 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው በቁጥጥር ስር በዋሉ በ21ኛው ቀን በተለዋጩ ቀጠሮ ቀን፣ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ የሰጠውን ውሳኔ አጽድቆ መዝገቡን ዘግቷል።
የዓለም አቀፍ ተቋማት ምላሽ
ጋዜጠኞቹ መታሰራቸውን ተከትሎ የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባልደረባዎች የሆኑት ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው እና አርታኢ ትዕግስት ዘሪሁን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ ጠይቋል።
የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ “የኢትዮጵያ ህዝብ በጤና ዙሪያ የሚቀርቡ ገለልተኛ ዘገባዎችን ማግኘቱ ወሳኝ ነው” ያሉ ሲሆን፣ “ባለሥልጣናት በዚህ ጉዳይ ላይ በሳንሱር እና በቁጥጥር ምላሽ መስጠታቸው እጅግ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ጋዜጠኞች የሆኑት ትዕግስት ዘሪሁን፣ ምንታምር ፀጋው እና እሸቴ አሰፋ ረቡዕ ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም የታሰሩት ጣቢያው የጤና ባለሙያዎችን የተመለከተ ዘገባ ካስተላለፈ ከጥቂት ቀናት በኋላ መሆኑን ጠቁሟል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ከነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በጋዜጠኞች እና በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው እስር በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ የፕሬስ ነፃነትን አደጋ ላይ ይጥላል ሲልም አስጠንቅቋል።