GridArt_20250924_214032711

የኢትዮጵያ ፕሬስ በሚዲያው ያወጣው ሀሰተኛ ዘገባ የቁጫ ብሔርን ተፈጥሯዊ፣ ህገ-መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚደፈጥጥ የህዝብ ክብር የነካ ነው ሲል ቁሕዴፓ አውግዟል።

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “የቁጫ ብሔር መባሉ ስህተት ነው” በሚል የሰራውን ዘገባ በተመለከተ ማምሻውን መግለጫ አውጥቷል።

ዳግም እርማት በሚል የተሰራ ዘገባ

ፓርቲው ይህ በሚዲያው አውጥቶ የነበረው ሀሰተኛ ዘገባ የቁጫ ብሔርን ተፈጥሯዊ፣ ህገ-መንግስታዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጥስና ከከትልቅ ሚዲያ የማይጠበቅ ኃላፊነት የጎደለው ጭፍን አካሄድ ነው ሲል ድርጊቱን ክፉኛ አውግዟል።

ፓርቲው በመግለጫው እንዳብራራው፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የቁጫ ብሔር ዘመን መለወጫ የሆነውን ‘ዎዳላ ጋዜ’ በዓል ከሌሎች በዓላት ጋር አካቶ ዘግቦ ነበር።

ይህ ዘገባ ከብሔሩ አባላት አድናቆት ካገኘ በኋላ ድርጅቱ ዘገባውን ከገጹ ላይ እንዳነሳውና፣ በኋላም “የቁጫ ብሔር መባሉ ስህተት ነው” የሚል ሌላ ዘገባ ማውጣቱን ገልጿል።

ፓርቲው ይህ ድርጊት የቁጫ ብሔር አባላትን ክብርና ሞራል የነካ ነው ብሏል።

ሚዲያው ዘግቦ የነበረውና ከገፁ በኃላ ያነሳው ዘገባ

ቁሕዴፓ አክሎም፣ የፕሬስ ድርጅቱ መረጃውን ያገኘሁት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን እና ከጋሞ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው ማለቱን በመጥቀስ፣ እነዚህ ተቋማት የብሔር ማንነትን የመወሰን ሥልጣን የላቸውም ሲል ተከራክሯል።

እንደ ፓርቲው ገለጻ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ፕሮፋይል በተመለከተ የመረጃ ምንጭ ሊሆን የሚችለው የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻ ነው።

በመጨረሻም፣ ፓርቲው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተላለፈውን ዘገባ በአስቸኳይ ከገጹ ላይ እንዲያነሳው፣ ለቁጫ ብሔርም ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቅ አጥብቆ አሳስቧል።

ፓርቲው መሰል ስህተቶች እንዳይደገሙ አሳስቦ፣ የሕዝቡን ክብር ለማስጠበቅ አስፈላጊውንና ሕጋዊውን መንገድ እንደሚከተል አስታውቋል።