1759421318864

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዎላይታ ዞን መዋቅሮች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታየው የአመራር ለውጥ (ሹም-ሽር) በአካባቢው ዘላቂ ልማት እንዳይኖር እና ተቋማዊ ትውስታ (Institutional Memory) እንዲጠፋ እያደረገ ነው ሲሉ ጉዳዩን የሚከታተሉ ግለሰቦች እና አስተያየት ሰጪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት በዞኑ መዋቅሮች ውስጥ መካሄዱን ተከትሎ አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመራሮች ‘ተሾመ’ ከተባለ በኋላ ብዙ ሳይቆይ ‘ተሻረ’ እየተባለ የሚሰማው ሁኔታ በአካባቢው የልማት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት፣ በሥራ አመራር ሳይንስ መርሆዎች መሰረት አንድ አመራር ውጤታማ ለመሆን፣ ተቋሙን ለማጥናት፣ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን ለመለየት፣ ለማቀድ፣ ሀብት ለማሰባሰብና የአጭርና የረጅም ጊዜ ትልሞችን ለይቶ ወደ ትግበራ ለመግባት ምክንያታዊ የሆነ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል።

ይሁን እንጂ፣ በዎላይታ አስተዳደር በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ታይቷል የተባለው “በዘመቻ የመሾምና በዘመቻ የመሻር አባዜ” ከዚህ መርህ ጋር የሚጋጭ ነው ተብሏል።

ተደጋጋሚ የአመራር ለውጥ የድርጅቶችን ልምድና ዕውቀት የሚያጠፋ በመሆኑ፣ ተቋማት ተረጋግተው ልማት እንዳይሰሩ ከቀውስ ወደ ቀውስ እየተገላበጡ እንዲከሽፉ ያደርጋል።

በሠራተኛውም ሆነ በአመራሩ ዘንድ የመታመንና ውጤታማ የመሆን ስሜት እንዲቀንስ ያደርጋል።

በልማት ሥራዎችና በመደበኛ አገልግሎቶች ላይ በሚፈለገው ጥራትና ሽፋን እንዳይሰጡ እንቅፋት ይፈጥራል።

“አሁን ሰዎች የሚሾሙት በምን መስፈርት ይሁን፣ የሚሻሩትም በምን ምክንያት ይሁን ህብረተሰቡ የሚያውቀው ነገር የለም። የምንሰማው እነ ‘ተሾመን’ እና ‘ተሻረን’ ብቻ ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

በአስተያየቱ መሰረት፣ የሚመለከተው አካል አመራርን የመሾምና የመሻር ስልጣን እንዳለው ሁሉ፣ የመደገፍና የማብቃት ኃላፊነት ጭምር እንዳለበት ተገንዝቦ አካሄዱን ሊያስተካክል ይገባል የሚል ጥሪ ቀርቧል።

Ethiopia #Wolaita #southethiopia