የእርዳታ ገንዘብ ዘረፋ ቅሌት: ፌዴራል ደህንነቶች ሦስት ቁልፍ የክልል አመራሮችን ሲይዙ፣ የክልሉ መግለጫው ያስነሳው ከባድ ጥያቄ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን የመሬት ናዳ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰበሰበውን የእርዳታ ገንዘብ ለማሸሽ የተደረገው ከፍተኛ የሙስና ሙከራ መጋለጡን ተከትሎ፣ የፌዴራል ደህንነት አካላት ሦስት ቁልፍ የዞን አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን WT Media አረጋግጦ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የጎፋ ዞን መንግሥት ዘግይቶ ያወጣው ማብራሪያ ደግሞ በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
WT Media ትናንት ማምሻውን በዘገበው መረጃ መሠረት፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ የተባሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከጎፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተክለማርያም በቀሌ ጋር በመሆን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሸሽ ከደላላ ጋር ተመሳጥረው ነበር።

የፌዴራል ደህንነቶችና የብሔራዊ ባንክ በጋራ በወሰዱት እርምጃ፣ ሦስት ቁልፍ የዞኑ አመራሮች ማምሻውን በሳውላ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፦
አቶ ተክለማርያም በቀሌ (የጎፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ)
አቶ ማርቆስ መለሰ (የጎፋ ዞን አደጋ ሥጋት መምሪያ ም/ኃላፊ)
ወ/ሮ አበበች ታዬ (የባንክ ቼክ አዘጋጅ)
የፌዴራል ደህንነቶች በተለይም ገንዘብ የማዛወር ሥራውን በቀጥታ ሲያመቻቹ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ላይ፣ አቶ ነፃነት ገመዳ (ደላላ) እና የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሆነው አቶ ጋንታ ጋምኣ (የአቶ ጥላሁን ከበደ የቅርብ ሰው) ላይ ጥልቅ ምርመራ ጀምረዋል።
አቶ ጋንታ ጋምኣ 48 ሚሊዮን ብር በአቶ ነፃነት ገመዳ አማካኝነት ወደ ነጋዴዎች አካውንት እንዲዛወር የማድረግ ሥራ መሥራታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ በመገኘቱ ክትትል እየተደረገባቸው ነው።
የፌዴራል የደህንነት አካላት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ተከትሎ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ከጎፋ ዞን የተሰጠ መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው 60,276,383 ብር ቀደም ሲል ተሠርቶ ቮይድ በተደረገ ቼክ አስመስሎ በማሳተም ገንዘቡን ለመዝረፍ የተሞከረ ሲሆን፣ አስተዳደሩ በሰጠው ጥቆማ ዘረፋው ሳይወጣ መክሸፉን አስታውቋል።
ሆኖም፣ ይህ መግለጫ ከኅብረተሰቡና ከፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ በርካታ አሳሳቢ ጥያቄዎችን አስነስቷል፦
“ሌብነቱን ያጋለጠውን WT Media መውቀሳችሁ ሌብነቱ ለምን ለምን ተጋለጠብን የሚል ትርጉም ይሰጣል” ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የዞኑ አስተዳደር ዘረፋውን በማስቆም ቀዳሚ ቢሆን ኖሮ ለምን ወዲያውኑ ለሕዝብ ይፋ አላደረገም ሲሉ ጠይቀዋል።
“ይሄ ሁሉ ገንዘብ እያለ ነው ተማሪዎች ሻራ ቤት ውስጥ የሚማሩት አሳፋሪ ነው” ሲሉ የሚተቹ ግለሰቦች፣ ተጎጂዎች ችግር ላይ እያሉ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከአንድ ዓመት በላይ ባንክ ላይ ምን ሲያደርግ ቆየ? የሚል ከባድ ጥያቄ አንስተዋል።
የዞኑ መግለጫ ከባንክ ቼክ ውጪ ከባንኩ ገንዘቡ ወጪ እንዲሆን ያዘዘውን ደብዳቤ በዝምታ ያለፈው ለምንድነው? ሲሉ የጠየቁት የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ “ከባንክ ቼክ ጋር አባሪ ተደርጎ ቀንና ቁጥር ተጠቅሶ በባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት ስምና ፊርማ የወጣው ደብዳቤ መዘለሉ ግን ትልቅ ጥርጣሬን ያጭራል” ብለዋል።

ይህ የማጭበርበር ሙከራ፣ የክልሉ አመራሮች ቀደም ሲል ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የእርዳታ ሀብት ለተጎጂዎች ሳይደርስ መመዝበሩን በተመለከተ WT Media ከወራት በፊት የዘገበውን ስጋት የሚያጠናክር ነው።
በአሁኑ ሰዓትም፣ ጥልቅ መረጃ በእጁ የሚገኘው አቶ ተክለማርያም በቀሌን ከሕግ ለማሸሽና ለመሰወር በጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ የክልሉን ፖለቲካ ተንታኞች፣ ዋናዎቹ የወንጀል አድራጊዎች የሆኑት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ከፍተኛ አመራሮች ተጠያቂነት ሊሰፍን ይገባል የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
“ከሙታን ላይ ዘርፎ የሚበላውን አመራር ከማውገዝ ይልቅ ሌብነቱን ያጋለጠውን WT ሚዲያ መውቀሳችሁ ሌብነቱ ለምን ለምን ተጋለጠብን የሚል ትርጉም ይሰጣል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ ቀርቧል።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media