የጋሞ ዞን ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ኅብረት ከ40 በላይ ፖሊስ ወደ ቤተክርስቲያኗ ዘልቀው በመግባት ወንጀል መፈፀሙን በመግለፅ የዞኑ አስተዳደር ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ጠይቋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ዞን ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽ/ቤት፣ የዞኑ ዋና አስተዳደር በኃይማኖት ተቋሙ የውስጥ ጉዳይ ላይ ሕገ መንግስታዊ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት እየፈጸመ ነው በማለት ከፍተኛ ተቃውሞውን ገልጿል።

ፖሊሶቹ ወደ ቤተክርስቲያኑ ዘልቀው በመግባት የሕግ የበላይነትን የሚያሳዩት ራሳቸው እንደሆኑ በመግለጽ በሠራተኞች ላይ ድብደባ፣ ማንገላታት እና ማስፈራራት የፈጸሙ ሲሆን፣ የኃይል እርምጃው ከተጠናቀቀ በኋላም የአንዳንድ ተቋሙ አመራሮችን በቁጥጥር ስር አውለው ወስደዋል ብሏል።
ኅብረቱ መስከረም 27/2018 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ፣ የዞኑ ዋና አስተዳደር ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመስጠት መስከረም 05/2018 ዓ/ም ከ40 በላይ የሚሆኑ የታጠቁ የፖሊስ አባላትን ወደ ጫሞ ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽ/ቤት በመላክ ድንገተኛ ክበባና የኃይል እርምጃ እንደተወሰደ አስታውቋል።


ፖሊስ ሠራዊቱ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር በሌለበትና ቤተ ክርስቲያኑ መደበኛ ሥራውን እየሠራ ባለበት ቅጥር ግቢው ውስጥ በኃይል ሰብሮ በመግባት የመንፈሳዊ አገልግሎቱን አደናቅፏል።
አባላቱ የፍርድ ቤት ማዘዣ እንዳላቸው ቢናገሩም፣ እንዲነበብ ሲጠየቅ የያዙት ጽሑፍ ኮፒ በመሆኑ የማይነበብ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኋላም ሄደው ያመጡት ማዘዣ ተቋሙን የማይመለከት የተሳሳተ አድራሻ እንደነበር ኅብረቱ በመግለጫው አመልክቷል።
የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደተመለከተው፦ ኅብረቱ በመግለጫው የችግሩ መንስኤ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለዓመታት የቆየ የመዋቅር ቅነሳ አለመግባባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ደንብ መሠረት መፈታት አለመቻሉ እንደሆነ ጠቁሟል።
ነገር ግን የጋሞ ዞን አስተዳደር አሁን ባለው ሁኔታ የመንግስትን ሥልጣን ጋሻ በማድረግ፣ ከዚህ ቀደም ጥፋት ይፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦችን ወግኖ “ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት” ሥራ ላይ ተጠምዷል ሲል ከሷል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይ በፍርድ ቤቶች እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ውሳኔዎች የተሰጡበት ቢሆንም፣ የዞኑ አስተዳደር “ፍርድ ቤቶች አሁን በእጄ ናቸውና ውሳኔዎችን እገለብጣለሁ” በማለት የኃይል እርምጃውን ወደ ግጭት በማስገባት የደቡብ ምዕራብ ቀጣና ፍላጎትን ለማሳካት እየሰራ ነው የሚል ከባድ ውንጀላ በመግለጫው ቀርቧል።
የጋሞ ዞን ቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽ/ቤት የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3ን (“መንግሥት በኃይማኖት ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም”) እና አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1-5ን በመተላለፍ እየተፈጸመ ያለውን ኢ-ሕገ መንግስታዊ ተግባር እንዲቆም አጥብቆ ጠይቋል።
በመጨረሻም፣ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ ጣልቃ በመግባት የሕግ የበላይነት በጋሞ ዞን እንዲከበር፣ ያላግባብ የታፈሱ የተቋሙ አመራሮች ከእስር እንዲለቀቁ እና ሁከት እንዲቆም እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media