GridArt_20251009_155041206

በቅርቡ ይከፈታል ተብሎ የነበረው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት የዎላይታ ምድብ ችሎት በጊዜ ባለመጀመሩ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እየተዳረገ መሆኑ ቅሬታ መፍጠሩ ተገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለዜጎች ተደራሽና የተፋጠነ ፍትሕ ለማምጣት ታስቦ በዎላይታ ሶዶ እና በአርባ ምንጭ ከተማ እንዲከፈት ተወስኖ የነበረው የምድብ ችሎት (Circuit Court) ተግባራዊ እንቅስቃሴ በእንጥልጥል ላይ መሆኑን ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ደግሞ የድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) የህግ ባለሙያዎቹ በሰጡት አስተያየት፣ በፍትሕ ዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምድብ ችሎቶችን በይፋ ለማስጀመር አቅዶ በነበረው ጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ተጨባጭ ዝግጅት አለማድረጉን ተችተዋል።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፣ ከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ የሆነው ይህ የምድብ ችሎት የመክፈት ውሳኔ መዘግየቱ በዋነኛነት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች ለዓመታት ለዘለቀው የፍትሕ ርቀት እና እንግልት መፍትሔ ለመስጠት ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ነው።

በተለይም በዎላይታ ሶዶ ከተማ የሚከፈተው ችሎት በቀድሞ ክልል ተደራጅቶ በተሟላ እና ዝግጁ በሆነ ቢሮ ላይ ሊመሰረት ሲችል፣ የሰው ኃይልና መዛግብትን በማዛወር ብቻ ሥራ መጀመር የሚቻልበት ሁኔታ እያለ፣ ፍርድ ቤቱ በጀት ጭምር የማይጠይቁ እንደ ዳኞችንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን መለየት፣ መዛግብትን ማደራጀት እና ቢሮዎች ላይ የዝግጅት እንቅስቃሴ አለማድረግ በመዘግየቱ ሦስት ወራትን የሚጠጋ ጊዜ ያለ ምንም ተግባራዊ ለውጥ አልፏል ብለዋል።

የተቋሙ አመራሮች ከመደበኛ ኃላፊነታቸው ውጭ በማይመለከታቸው አስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይ ጊዜያቸውን በማጥፋት ፍርድ ቤቱ ሥራ ሲጀምር ህዝቡ ዳግም ለከፍተኛ ወጪ እና እንግልት ሳውላ እንዲጓዝ ሊገደድ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዎላይታ ምድብ ችሎት የሚገባበትን የሕንጻ እድሳትና የጥገና ሥራ የደረሰበትን ደረጃ መጎብኘታቸውን አስታውቋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ምድብ ችሎት ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው” የሚሉ መግለጫዎችን ከማውጣት ውጪ በተግባር ለውጥ የማያሳይበት ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።

በቀድሞ ወርም ቢሆን ተመሳሳይ መግለጫዎች መሰጠታቸው፣ አሁንም ተመሳሳይ መረጃ መሰጠቱ ተግባራዊ ለውጥ የማይመጣባቸውን ወሬዎች ብቻ እያሰራጨ መሆኑን ይጠቁማል ብለዋል።

ባለሙያዎቹ በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ የምድብ ችሎቱ እንዲከፈት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምክረ-ሐሳብ ሰጥተዋል።