GridArt_20251009_202025047

ዎሕዴግ በዎላይታ ድንበር ላይ አዲስ እና የተደራጀ ‘የመሬት ወረራ’ እየተፈጸመ ነው በሚል ለመንግሥት አስቸኳይ ጥሪ አቀረበ

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ከሲዳማ ክልል በዎላይታ ድንበር ላይ በርካታ ሰዎች ድንበር በመሻገር የመሬት ወረራ እየፈጸሙ እና የዎላይታ ተወላጆችን ከቀያቸው እያፈናቀሉ መሆናቸውን በመግለጽ የአቋም መግለጫ ማምሻውን አውጥቷል።

ፓርቲው ይህንን ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ለፌዴራል፣ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም ለዎላይታ ዞን አስተዳደሮች ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።

ዛሬ ማምሻውን በመስከረም 29/2018 ዓ.ም. የተሰጠው የዎሕዴግ መግለጫ እንዳመለከተው፣ በቅርቡ እየተፈጸመ ያለው የመሬት ወረራ በ2017 ዓ.ም. ሲዳማ በኩል በመንግሥት አመራሮች ይደገፍ የነበረና የክልሉን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በማስከተል ዎላይታውያንን ከትውልድ ቦታቸው አፈናቅሎና ገድሎ የነበረው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የመጣ እንደሆነ የገለፀውን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) ተመልክቷል።

የአቋም መግለጫው የሚከተሉትን አስረጂ ነጥቦች ያጠቃልላል፡

ፓርቲው ከሥፍራው ባገኘው መረጃ፣ አሁን እየተፈጸመ ያለው የመሬት ወረራ ከዚህ በፊት ከነበረው “እጅግ የከፋና የተደራጀ” ከመሆኑም በላይ የታጣቂ ኃይሎች እገዛ ታክሎበት እንደሆነ ገልጿል።

በርካታ ሰዎች ከሲዳማ በኩል ወደ ዎላይታ ድንበር በመሻገር የመሬት ወረራ ከመፈጸማቸው ባሻገር፣ የዎላይታ ሕዝብ ከቀዬው እየተፈናቀለ መሆኑን የሚያሳይ በማስረጃ የተደገፈ “የይድረሱልኝ” ጥሪ ለፓርቲው ጽ/ቤት እየደረሰ ይገኛል።

በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር ዓላማ ባለው በተደራጀ መንገድ ትንኮሳ የሚፈጽሙ አካላት በብዛትና በተናበበ መልኩ ከሲዳማ ወደ ዎላይታ ድንበር እየተሻገሩ መሆኑ ድርጊቱን “ከወትሮ ለየት” ያደርገዋል ብሏል።

ዎሕዴግ የዎላይታ ዞን መንግሥት፣ የሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት፣ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ እና በሕዝቡ ላይ የከፋ ችግር ሳይፈጠር በፊት ሕዝቡን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲው በተጨማሪም እየተፈጸመ ያለውን የመሬት ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ በጥብቅ አሳስቧል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media