1760113187159

ባንኩ በጎፋ የመሬት ናዳ ተጎጂዎች የተሰበሰበ 60 ሚሊዮን ማጭበርበር በተመለከተ ተጠይቆ “እኛም እንደማንኛውም ሰው ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው ያየነው፣ ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የለንም” አለ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን የመሬት ናዳ ተጎጂዎች የእርዳታ ገንዘብ ላይ የተፈጸመው የ60 ሚሊዮን ብር ዘረፋ ሙከራን ተከትሎ፣ የፌዴራል ደህንነቶች ሦስት ቁልፍ የዞን አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውንና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ዝርዝር መረጃዎችን በተደጋጋሚ WT Media መዘገቡ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ፣ ገንዘቡ ለመውጣት ሞክሯል በተባለበት ባንክ የተሰጠው ምላሽ እና የልዩ ተጠርጣሪው አያያዝ፣ ጉዳዩን አወዛጋቢ አድርጎታል።

የዘረፋው ሙከራ ተፈጽሟል የተባለው በአዲስ አበባ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ እንደሆነ የጎፋ ዞን መንግሥት መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ይሁንና WT Media በዛሬው ዕለት የባንኩን ሥራ አስኪያጅ በቀጥታ አነጋግሮ አዲስ መረጃ አግኝቷል።

የንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ምላሽ ሲሰጡ፣ “በእኛ ባንክ ቅርንጫፍ በተባለው ግለሰብና 60 ሚሊዮን ብር ተብሎ በተጠቀሰው ገንዘብ መጠን ለማጭበርበር የመጣ ሰው አላየንም” ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም “እኛ ስለጉዳዩ እንደማንኛውም ሰው ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው ያየነው፣ እኛ ጋ ያንን በተመለከተ ምንም መረጃ የለንም” ሲሉ፣ መረጃው ከክልሉ መንግሥት መግለጫ ጋር የሚጋጭ ሆኗል።

በተጨማሪም “ጉዳዩን በተመለከተ ለማነጋገር የሚፈለግ የትኛውም ሚዲያ በአካል መጥቶ መጠየቅ ይችላሉ” በሚል ሥራአስኪያጁ ሀሳቡን አካፍለዋል።

በሐሰተኛ ቼክ ገንዘቡን ለማውጣት ሞክሯል የተባለው ግለሰብ “መሐመድ ኑርሁሰን ሲራጅ” በተመለከተ WT Media ያደረገው ተጨማሪ ማጣሪያ፣ በርካታ ጥርጣሬዎችን አስነስቷል።

ግለሰቡ ወንጀሉ በተፈፀመበት አዲስ አበባ ሳይሆን፣ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ እንደታሰረ ይነገራል።

“መሐመድ ኑርሁሰን ሲራጅ” የተባለውን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች በተለየ “በብቸኝነት በተለየ ክፍል ታስሯል” እና “ማንም እንዲጠይቀው አይፈቀድም”።

በሌላ በኩል፣ በጉዳዩ ዙሪያ የታሰሩት አመራሮችን (አቶ ተክለማርያም በቀሌን፣ አቶ ማርቆስ መለሰን እና ወ/ሮ አበበች ታዬን) ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው በነፃነት እየጠየቁ እንደሆነ ከቦታው የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

አንድ የሕግ ባለሙያ ለWT Media ( ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ) እንደገለጹት፣ ሁኔታው “ሕገወጥና እውነታውን ለመደበቅ የሚደረግ ሩጫ” ነው። ግለሰቡ በሐሰተኛ ቼክ ገንዘብ ለማውጣት ቢሞክር ባንኩ በሕግ አግባብ የመክሰስ ግዴታ አለበት።

ባንኩ በወንጀል ድርጊት የተፈፀመበት ተቋም እንደመሆኑ ዝም ማለቱ አጠያያቂ ነው ሲሉ “ድርጊት በባንኩ ላይ ተፈጽሟል” የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በሰጠው መግለጫ ዘረፋው “በአስተዳደሩ ጥቆማ” መክሸፉን ቢያስታውቅም፣ ከኅብረተሰቡና ከፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ በርካታ አሳሳቢ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የዞኑ አስተዳደር ዘረፋውን በማስቆም ቀዳሚ ቢሆን ኖሮ “ለምን ወዲያውኑ ለሕዝብ ይፋ አላደረገም?” ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል፤ “ሌብነቱን ያጋለጠውን WT Media መውቀሳችሁ ሌብነቱ ለምን ለምን ተጋለጠብን የሚል ትርጉም ይሰጣልም” ብለዋል።

ተጎጂዎች ችግር ላይ እያሉ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ “ከአንድ ዓመት በላይ ባንክ ላይ ምን ሲያደርግ ቆየ?” የሚለው ከባድ ጥያቄ መልስ አላገኘም።

በተፈጠረው ቅሌት ዙሪያ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በሕግ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ሥራ መጀመሩን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ገጽታ ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ተናግረዋል።

በተጨማሪም፣ “ከጉዳዩ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው በተጠረጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ላይ ክትትል እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።

ቀደም ሲል በሙከራው ውስጥ ቁልፍ ተሳታፊነት አላቸው የተባሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ሰዓትም ጥልቅ መረጃ በእጁ የሚገኘው አቶ ተክለማርያም በቀሌን እንዲሁም በስሙ ቼክ የተፃፈለት ማንነቱ ለጊዜው ያልተለየ “መሐመድ ኑርሁሰን ሲራጅ” የተባለውን ከሕግ ለማሸሽና ለመሰወር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ የደረሰን ተጨባጭ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media