GridArt_20251015_214759607

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመልካም አስተዳደር እጦት የወለዳቸው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተበራከቱ መሆኑን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጿል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የተመራ ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅና አያያዝ ዙሪያ በዛሬው ዕለት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ግምገማ አካሂዷል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ

ከግምገማው በኋላ የኮሚሽኑ ልዑክ በክልሉ ‘ከፍተኛ ድክመት’ መታየቱንና ‘የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተበራከቱ’ መሆኑን ማሳሰቡን WT Media ከውስጥ ምንጮቹ አረጋግጧል።

የኮሚሽኑ ልዑክ በክልሉ በተደጋጋሚ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚደርስባቸውን የቁጫ፣ ዘይሴ፣ ጉማይዴና ኮንሶ ሕዝቦችን ጨምሮ፣ የተደራጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን አረጋግጧል።

የኮሚሽኑ ቡድን አባላት ትዝብታቸውን ለWT Media ሲያጋሩ፣ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ ለተመዘገበው የፍትሕ እጦት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት፣ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በጊዜ አለመክፈል፣ ሥር የሰደደና የተጠላለፈ ሌብነት፣ ዜጎችን እንደፈለጉ ማሰር፣ ማሰቃየት፣ ፍርድቤት አለማቅረብ እንዲሁም ቡድንተኝነትና ጫፍ የወጣ ጎሰኝነት የክልሉ መሪዎች ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።

ቡድኑ “በሕዝብ ሀብት ላይ የሚፈነጩ የፊት አመራር መብዛትና ጠያቂ ትውልድ ማሰርና ማሳደድ የበዛበት ክልል” ሲል ክልሉን ፈርጇል።

ለጉብኝትና ለግምገማ የመጡ ልዑካን ቡድን

በማረሚያ ቤቶች እና በጊዜያዊ ማቆያ የታራሚዎች አያያዝ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑንም አረጋግጧል።

ኮሚሽኑ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች አጋር አካላት ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

በተቃራኒው በክልሉ ኮሙኒኬሽን በኩል በወጣ ዘገባ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ከኢሰመኮ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ጋር መወያየታቸውን ገልጸው፣ የክልሉ መንግሥት ለዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ‘ቁርጠኛ ነው’ ማለታቸውን ዘግቧል።

አቶ ጥላሁን “ሕጋዊና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን መሠረት በማድረግ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ እና ለዜጎች ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ መከበር አበክሮ በመስራት ላይ” መሆናቸውን ለኮሚሽኑ ልዑክ እንደገለጹ ተጠቅሷል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድሩ “የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ቀጠናውን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ የጥፋት ኃይሎች” መኖራቸውን ጠቅሰው፣ መንግሥት ዜጎችን ከእነዚህ ኃይሎች በመጠበቅ ሰብዓዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ማረጋገጣቸውን ዘገባው ይገልጻል።

ይህ የዛሬው የኢሰመኮ ግኝት፣ WT Media ቀደም ሲል በተደጋጋሚ በክልሉ በአመራሩ እየተፈፀመ ነው ሲል የተለያዩ መረጃና ማስረጃ አስደግፎ በዘገባቸው የፖለቲካ ሴራዎች፣ የገንዘብ ምዝበራዎች እና በፓርቲ አባላት ላይ እየደረሰ ነው በተባለው ድብደባና እስር ዙሪያ የቀረቡትን ስጋቶች ያጠናክራል።

አቶ ጥላሁን ከበደ ክልሉ ለሕግ የበላይነት ቁርጠኛ ነው ማለታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢሰመኮ ‘ከፍተኛ ድክመት’ መኖሩን ማረጋገጡ በክልሉ ውስጥ ስር የሰደደውን የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት መጓደልና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግር አመላካች ነው በሚል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media