ኬኒያዊያን በ60 ዓመት ያሳኩትን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ኢትዮጵያውያን በ3ሺህ ዓመታት ጉዞ ለምን አላሳኩም !?
አንጋፋው ኬኒያዊ ፖለቲከኛ፣ ለዴሞክራሲና ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሕይወት ዘመናቸውን የሰጡት ክቡር ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ (Baba)፣ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ፣ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው በትውልድ መንደራቸው ቦንዶ (Bondo) በታላቅ ክብርና ድምቀት በዛሬው ዕለት ተፈፅሟል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት መላው የኬንያ ሕዝብ በፖለቲካ ልዩነት ሳይከፋፈል ለመሪው የገለፀው ጥልቅ ሀዘን፣ ራይላ ኦዲንጋ በሰላማዊ ትግላቸው ያመጡትን ከፍተኛ ለውጥ እና የሕዝብ ተቀባይነት በድጋሚ ያረጋገጠበት ወቅት ነበር።
ራይላ ኦዲንጋ ከሉዋ ጎሳ ተወልደው፣ የሕይወት ዘመናቸውን ሙሉ ከገዢው መንግስት በተፎካካሪነት ቆመው ሰላማዊ ትግልን ብቻ በመከተል፣ እንዴት በመላው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ስኬታማ የፖለቲካ መሪ ሊሆኑ ቻሉ? ቁልፉ ያለው ኬንያ በፖለቲካ ባህሏ ውስጥ ባስመዘገበችው ብስለት መሆኑን ያሳያል።




የኬንያ የፖለቲካ ልዕልና ቁልፍ ምስጢሮች፦
በኬንያ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት ፈፅሞ አይታሰብም። ልዩነቶች የሚፈቱት በሰላማዊ ውይይት እንጂ በመሳሪያ አይደለም።
ዜጎች መንግስትን በአደባባይ የመተቸት ሙሉ ዕድል አላቸው። “ለምን ተናገርክ” ተብሎ እስር የለም። ሚዲያዎች ያለ ጣልቃ ገብነት የተቃዋሚዎችን ሰልፍ በቀጥታ ያሰራጫሉ፣ አይዘጉም፣ ጋዜጠኞችም አይታሰሩም። መንግስት ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ዜጎችን የመጠበቅ ሃላፊነቱን ይወጣል።
ከ45 በላይ የተለያዩ ብሔሮች ባሉባት ኬንያ የብሔር ጥላቻ ሆነ ግጭት አይታሰብም። ፖለቲከኞች የሚወዳደሩት በብሔር ኮታ ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት ነው።
ኬንያ በአፍሪካ ጦርነት የማይካሄድባት፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ያላት፣ በሁሉም አከባቢዎች ፍትሀዊ የመሠረት ልማት የገነባች፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ስደተኞች ምቹ የሆነች የነፃነት ምድር ሆናለች።
ይህ ሁሉ ሰላም ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን፣ እንደ ራይላ ኦዲንጋ ያሉት መሪዎች ለዘመናት በከፈሉት ሰላማዊ ትግል ፍሬ ውጤት ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ልዩነትን በጦርነት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት፣ ፖለቲከኞች በሀሳብ የሚወዳደሩበት፣ ሚዲያዎችና ዜጎች በነፃነት የሚገልፁበት፣ ልማት በፍትሀዊነት የሚገነባበትን እና ከጎረቤቶቿ ጋር በፍቅር የምትኖርበትን የላቀ ተሞክሮ ከኬንያ መቅዳት ይኖርባታል።
ኢትዮጵያ በየወቅቱ በሃሳብና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ወደ ጦርነት ሜዳ እየገባች ገንዘቧን ከማውደም እና የዜጎቿን ሕይወት በከንቱ ከማሳለፍ ይልቅ፣ ሩቅ ሳንሄድ ከጎረቤት ኬንያ የሰላም ፖለቲካ ትምህርት በመውሰድ ወደ ዕድገት እንመለስ።👐

ለታላቁ መሪ ለራይላ ኦዲንጋ (Baba) ቤተሰቦች እና መላው የኬንያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን😭
Tunatoa pole zetu za dhati kwa familia ya kiongozi mkuu, Raila Odinga (Baba), na taifa zima la Kenya 😭