GridArt_20251016_151034591

በዘይሴ ብሔረሰብ ‘የዘር ማጥፋት’ እየተፈጸመ ነው ተብሎ በተከሰሰበት አካባቢ ጦርነት ተከፈተ፤ የታሰሩ ዘይሴ ተወላጆች ‘ስንቅ እንዳይገባላቸው ተከልክሏል’ ተብሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ውስጥ በዘይሴ ብሔረሰብ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመባባሱም በላይ፣ በዛሬው ዕለት (ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም.) የክልሉ ልዩ ኃይል እና የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ከፍተኛ ጦርነት ከፍተው ውጊያ ላይ መሆናቸውን WT Media ከስፍራው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል።

የዘይሴ ነዋሪዎችና ምሁራን ቀደም ሲል “የዘር ማጥፋት (Genocide) መስፈርትን ያሟላል” ሲሉ የተከሰሱበት ይህ ድርጊት፣ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ተኩስ ልውውጥ ወደ ግጭት መግባቱ ተገልጿል።

የዘይሴ ሕዝብ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ራስን በራስ በልዩ ወረዳ መዋቅር ለማስተዳደር በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን የሚታወቅ ሲሆን፣ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮም በአካባቢው የፀጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ መምጣቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል። አሁን ላይ ግን የጋሞ ዞን አመራሮች የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ሽፋን በመጠቀም በሕዝቡ ላይ የኃይል እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለ WT Media ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በጋሞ ዞን ግዞላ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ታፍነው የታሰሩት 42 የዘይሴ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ መሆኑን ቤተሰቦችና የሕዝብ ተወካዮች ገልጸዋል።

ታሳሪዎቹ “ስንቅ እንዳይገባላቸው ተከልክለዋል” እንዲሁም ቤተሰብ እንዲጠይቃቸው አይፈቀድም። ቤተሰብ ለሽንት ውጭ በሚወጡበት ጊዜ ከሩቅ ቆመው እንዲያዩ ብቻ እንደተፈቀደላቸው ታውቋል።

እስሩን ሸሽተው ከአርባ ምንጭ አካባቢ ተከራይተው ለመኖር የሄዱ የዘይሴ ተወላጆች ቤት እንዳይከራዩ ክልከላ እየተደረገባቸው ነው። የጋሞ ዞን ፖለቲከኞችና ፖሊሶች ሲቪል ልብስ ለብሰው እየጠየቁ ከተከራዩበት እያስወጡ ይገኛሉ ተብሏል።

ቀደም ሲል የዘይሴ ደንብሌ ጤና ጣቢያን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ቀበሌዎችንና ማዘጋጃ ቤቶችን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት የክልሉ ልዩ ኃይልና ሌሎች ጸጥታ አካላት ካምፕ በማድረግ ተቋማቱን እየተጠቀሙበት መሆኑን WT Media ዘግቦ ነበር።

የዘይሴ ተወላጆች በጋሞ ዞን ካድሬዎችና ጨቋኞች እየደረሰ ያለው በደል “ለይቅር የማይባል ለትውልድ የሚቀመጥ” መሆኑን ገልጸው፣ “ተርቦ፣ ተጠምቶ የሞተ የለም። ግን ሲያልፍ ያስተዛዝባል” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

“በእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ዘይሴ ሕዝብን ማንበርከክ አይቻልም” ያሉት ተወካዮች፣ “ዘይሴ ተወላጆች ሕይወታቸውን መስዋዕት ማድረግ ጀምረዋልና በሕይወት መስዋዕትነት የዘይሴ ሕዝብ ነፃነት እውን ይሆናል” ብለዋል።

“ይህ ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጋሞ ዞን ጭቆና ነፃ የሚያወጣን ይሆናል… በሕይወት ዋጋ ነፃ እንወጣለን” በማለት ትግላቸው የመጨረሻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዘይሴ ሕዝብ የፌዴራል መንግሥት በአስቸኳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጣልቃ በመግባት፣ ሰላማዊውን ሕዝብ “ከተደቀነው ዘር የማጥፋት ዘመቻ እንዲታደገው” ጥሪ አቅርቧል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media