1000080855

ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ለአካባቢው ሕብረተሰብ፣ ለኢትዮጵያዊያን እና ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጤና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል (Sodo Christian Hospital) በአሁኑ ወቅት በአስተዳደራዊ ችግሮችና የሙስና ስጋቶች ሳቢያ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት መዘጋት ሊገጥመው ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የሆስፒታሉ ታማኝ የውስጥ ምንጮች ለWT Media አስታውቀዋል።

ሆስፒታሉን በመሰረቱት በዶ/ር ቀለሙ ደስታና በአሜሪካዊው ዶ/ር ሃሮልድ አዶልፍ መሪነት እንዲሁም በወቅቱ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በአቶ ደሣለኝ ኢኖሬ አመራር ዘመን እጅግ አመርቂ ውጤት ሲያስመዘግብ እንደነበር የሚገለጽ ሲሆን፣ ሆኖም ግን የሆስፒታሉን መሥራችና አንጋፋ ሚሲዮናዊያን የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎት አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የቁጥጥርና የተጠያቂነት ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት አደጋ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

ለሆስፒታሉ የቁልቁለት ጉዞ እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው ተቋሙን በበቂ ሁኔታ የሚቆጣጠር የኦዲትና ‘Check and Balance’ ሥርዓት አለመኖሩ ሲሆን፣ ይህም በጥቂት የአስተዳደር ሠራተኞች እጅ ወድቆ ለተጠያቂነት የራቀ አሠራር እንዲፈጠር መንገድ እንደከፈተ ተጠቁሟል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፦

ጨረታ የሌላቸው ግዢዎችና የዋጋ ማጋነን:

ግዢዎች – በተለይም የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ፣ የካፌ እና የንጽህና አገልግሎት ግዢዎች – ያለጨረታ እና በአስተዳደሩ ብቻ ይሁንታ እየተፈጸሙ እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ደግሞ ለተጋነነ የዋጋ ምዝበራ እና ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል።

ሐሰተኛ ደረሰኞችና ወጪዎች:

የተጭበረበሩና በሐሰተኛ የገንዘብ ደረሰኝ የተዘጋጁ ግዢዎች ወጪ ተደርገው መቅረባቸው ተጠቁሟል። በተጨማሪም ለሠራተኞች የተከፈለ የተጋነነ ክፍያዎች በግለሰቦች ፈቃድ ብቻ እየተፈጸሙ መሆኑ ተወስቷል።

የፌዴራል ታክስ ቅጣት:

በብልሹ አሠራር ምክንያት የፌዴራል ታክስ ኦዲት የሐዋሳ ቅርንጫፍ መ/ቤት ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ ከፍተኛ ቅጣት በመጣል ሆስፒታሉን ለከፋ ጉዳትና የመዘጋት አደጋ እንደዳረገው ተገልጿል።

ሆስፒታሉ ባለቤቶችም ችግሩን አድበስብሰው ሪፖርት ማቅረባቸውና ቅጣቱን “በልመና ከመጣው ገንዘብ እንከፍላለን” በማለት ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ መስጠታቸው ብዙዎችን እንዳሳዘነ ታውቋል።

የሠራተኞች መብት ጥሰትና ሞራል መጉደል:

የሆስፒታሉን ምሰሶ የሆኑ አንጋፋ ሠራተኞች በአሁኑ ወቅት በጥቂት ግለሰቦች ፍቃድ የሚባረሩበት አቤት ማይባልበት ተቋም እየሆነ ከመጣ ሰንብቷል ተብሏል።

በተጨማሪም አብዛኞቹ ሠራተኞች ከድካማቸው በታች ደመወዝ የሚከፈላቸው ሲሆን፣ የመንግስትን የደመወዝ ጭማሪ ለማስተካከል ፈቃደኛ አለመሆን በሠራተኞች መካከል ከፍተኛ ቅሬታንና ሞራል መጉደልን ፈጥሯል።

ይህን ተከትሎ ጥቂት የአስተዳደር ሠራተኞች ከመቶ ሺህ ብር በላይ ተከፋይ መሆናቸው ቅሬታውን አባብሶታል።

በመሆኑም ችግሮቹ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ስም ሽፋን እየታለፉ በመሆኑ ለህልውና አደጋ መዳረጉን ያመለከቱት ምንጮች፣ የዎላይታ ሕዝብ፣ እንዲሁም የሆስፒታሉ ባለቤቶችና የአገር ሽማግሌዎች ይህንን ተቋም ከመዘጋት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሕብረተሰቡ በተለይም የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ የሙስና ተጋላጭነቶችን በቅርበት እንዲከታተል፣ ለሕዝብ ተብሎ በልመና የመጣውን ገንዘብ አጠቃቀም እንዲያጣራና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር መኖሩን እንዲያረጋግጥ ጠይቋል።

በመጨረሻም፣ የሆስፒታሉ ባለቤቶች የአስተዳደር ክፍሎችን እንዲፈትሹ፣ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስዱና ተቋሙ ከውድቀትና ከመዘጋት እንዲድን ጥሪ ቀርቧል፤ የችግሩ ተከታታይ ሂደትም ለሕዝብ ይቀርባል ተብሏል።

ይህ ዘገባ በውስጥ ምንጮች በተሰጠ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ሌሎች አካላት እና የሆስፒታሉ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ሲደርሰን የምናቀርብ ይሆናል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media 

Read

“ሆስፒታሉ የህልውና አደጋና የ