1000081011

በጋሞ ዞን ከቤተክርስቲያን አገልግሎት መድረክ ላይ አስወርደው በማገት የተወሰደውን ጨምሮ 7 ግለሰቦች የገቡበት እስካሁን አልታወቀም ተብሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት “ኮማንድ ፖስት ነው” በሚል ሽፋን ከጋርዱላ ዞን ዴራሼ ወረዳ ሆልቴ ቀበሌ ሰባት ግለሰቦች በመንግሥት የጸጥታ ኃይል ታግተው ከተወሰዱ በኋላ እስከ ዛሬ የደረሱበት አለመታወቁን የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ለ WT Media (ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ) ገልጸዋል።

ቤተሰቦቹ በክልሉ ባሉ እስር ቤቶች ሁሉ በመፈለግ ምላሽ ማጣታቸውን በመግለጽ፣ የልጆቻቸውና የዘመዶቻቸው አካላዊ መገኛ እንዲገለጽላቸው በአጽንኦት ጠይቀዋል።

ታግተው የደረሱበት ያልታወቁት ሰባት ግለሰቦች የሚከተሉት ናቸው።👇

👉 አቶ ዮሐንስ ታገል
👉 አቶ ዳቆን ታምራት
👉 አቶ አልታዬ ከሐይበና
👉 በግዱ ግዛው
👉 ጀግናው ጀንበር
👉 ናሆም ጉይታ
👉 ሰብስቤ መሸሻ

ከታጋቶቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ታገል በቀን 24/12/2016 ዓ.ም. ከሆልቴ ከኢየሱስ ድንቅ ሥራ ቤተክርስቲያን ለኮንፍረንስ ተጠርተው ወደ ጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ እግዚአብሔር ተዋጊ አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ተጋብዘው በሄዱበት፣ ከአገልግሎት መድረክ ላይ ኃይሎች አውርደው እንደወሰዷቸው ቤተ ዘመዶቹ ተናግረዋል።

ቤተሰቦቹ በድንገተኛው የሰው መታገት ምክንያት በዘግናኝና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመግባት “በባዶ መዳፍ ላይ እንደወደቁ” ገልጸዋል።

በተመሳሳይም በዚያው ዕለት ከጋርዱላ ዞን መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ታግተው የተወሰዱ ግለሰቦችም ምንም ፍንጭ እንዳልተገኘባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

የግለሰቦቹ ቤተሰቦችና ምንጮች በሰጡት መግለጫ፣ የአካባቢው የጸጥታ ችግር ከ2014 ዓ.ም. የመዋቅር ጥያቄ ጋር ተያይዞ እርቅ ተፈጽሞ የነበረ ቢሆንም፣ አካባቢው እንዳይረጋጋ ሆን ብለው የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ይወቅሳሉ።

“በነፍስ ግድያና በሌብነት ተጠርጥረው የተከሰሱ ግለሰቦች በክልሉ መንግሥት ተሹመው” አካባቢው እንዳይረጋጋ በምሁራን መካከል ጭምር ክፍፍል እየፈጠሩ መሆኑን ክስ አቅርበዋል።

“የፈለጉትን ያስራሉ፣ የፈለጉትን ያሳድዳሉ፣ ሌሎችን ያስገድላሉ” የሚሉት ወገኖች፣ ሕዝቡ ፍትሕ ተነፍጎት “ፍትሕ ይሰጠን” በሚል ድምፁን ለሚመለከተው አካል እያሰማ እንደሆነ ገልጸዋል።

WT Media በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዜጎች መጥፋት እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የፌዴራል መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ታግተው የተወሰዱት ሰባት ዜጎች ያሉበትን እንዲገልጹ እና ለቤተሰቦቻቸው የፍትሕ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media