1000081147

ርዕሰ መስተዳድሩ “የዕርዳታ ገንዘብ ስርቆት ጨምሮ በሌሎች ቀጥታ የተሳተፉ ግለሰቦችን ከተጠያቂነት ለማስመለጥ የኃላፊነት ቦታ መቀየርና በጡረታ እንዲወጡ” እያደረጉ መሆኑ ተገለፀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ከዚህ ቀደም WT Media የዘገበውን “የሌብነት ሰንሰለት” ለመሸፈንና የቅርብ ተባባሪዎቻቸውን ከተጠያቂነት ለማስመለጥ የኃላፊነት ሽግሽግና ጡረታን እንደ ዘዴ እየተጠቀሙ መሆናቸው ተጋልጧል።

ይህ አዲስ መረጃ የሚያሳየው የሙስናው ሰንሰለት በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች ከተለያዩ አካላት ከተሰበሰበው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የእርዳታ ገንዘብ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ አቶ ጋንታ ጋምኦን ከአደጋ ስጋት ሥራ አመራርና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ኃላፊነት በማንሳት በጡረታ እንዲገለሉ በማድረግ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳትፎ ባደረገው ግለሰብ በመተካት፣ የዘረጉትን የሌብነት ሰንሰለትና ተጠያቂነት ለመሸፈን መሞከራቸው ተነግሯል።

አቶ ጋንታ ጋምኦ ኮሚሽነር በነበሩበት ወቅት፣ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ላይ በተከሰተው የመሬት ናዳ ምክንያት ከተለያዩ ወገኖች የተሰበሰበውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከፕሬዝዳንቱ በተሰጠው “ቀጭን ትዕዛዝ” ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ያሸሹትና ተከፋፍለው የተባሉ መሆናቸው ተገልጿል።

ገንዘቡን ለማውጣት በመንግሥት ተቋማት ሥም የታተመውን ቼክ፣ ምንም ዓይነት ውልና ሰነድ በሌለበት ሁኔታ የውስጥ ፈራሚ የፋይናንስ ባለሞያዎችን በማስፈራራት አስፈርመው፣ ምንም ነገር ያልተጻፈበትን ቼክ እራሳቸው እየሞሉ ለፕሬዝዳንቱ ቅርብ ለሆኑ ግለሰቦች ሲያድሉ እንደነበር መረጃው ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም ለጎፋ ወገኖች ከተሰበሰበው 60 ሚሊዮን ብር ከባንክ ለማውጣት ሲሞክሩ የተያዙ ግለሰቦች ላይ ክልሉ ዝምታን መምረጡ፣ ርዕሰ መስተዳድሩ ተባባሪዎቻቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን እየሰሩ መሆኑን ያመላክታል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የሚመራው የሙስና ሰንሰለት ከዕርዳታ ገንዘብ እስከ ሕንፃ ግንባታ ድረስ የተዘረጋ ሲሆን፣ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ ይህንን ሰንሰለት ለመሸፈንና በሙስናው ጉዳይ በቀጥታ የተሳተፉ ሰዎችን እንዲሁም በከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ ግለሰቦችን ከተጠያቂነት ለማስመለጥ ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት ወደ ሌላ መስሪያ ቤት መቀየር፣ የኃላፊነት ሽግሽግ፣ በጡረታ እንዲወጡ ማድረግ እና ሌሎች ዘዴዎችን እንደመሳሪያ እየተጠቀሙበት መሆኑ የሕዝቡን አመኔታ በክልሉ መንግሥት ላይ በእጅጉ እንዲጠፋ አድርጓል።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media