1000081570

በዎላይታ የተከሰተውን ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ በቀላሉ መቆጣጠር የሚቻል ቢሆንም ለጤና መከላከል የተመደበው ገንዘብ ለፖለቲካ አላማ ስለሚውል እንቅፋት መፍጠሩን የጤና ባለሙያዎች አጋልጠዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን በርካታ ወረዳዎች ላይ የተከሰተውና “ከጦርነት በላይ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈና እያሰቃየ” ነው የተባለው የወባ ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከጤና ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት ባገኘው ዝርዝር መረጃ አረጋግጧል።

ወረርሽኙ በተለይም በ ዱጉና ፓንጎ፣ ሶዶ ከተማ፣ ቦሎሶ ቦምቤ፣ ክንዶ ኮይሻ፣ ክንዶ ዲዳዬ፣ ዳሞት ፑላሳ፣ ሁምቦና አባላ፣ ቦሎሶ ሶሬ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቷል።

በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መሠረታዊ የሚባሉ የሕክምና ቁሳቁስ ባለመኖሩ የብዙ እናቶችና ሕፃናት ሕይወት ማዳን እየተቻለ እየሞቱ መሆኑን ዶክተሮችና ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ወረርሽኙ ቀደም ሲል ወባ ተከስቶ በማይታወቅባቸው የዎላይታ ደጋማ ክፍልን ጨምሮ በመስፋፋቱ፣ ሁኔታው “በጣም አስደንጋጭ” እንደሆነ ተናግሯል።

የጤና ባለሙያዎች እና ዶክተሮች ለ WT Media በሰጡት መረጃ መሠረት፣ በወረርሽኙ መከሰት ጀርባ የከፋ የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና አለ።

ለሕብረተሰቡ ጤና አጠባበቅ ሲባል በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚመደበው ገንዘብ ለሌላ ዓላማ እየዋለ ነው። ገንዘቡ “ለፖለቲካ ስራዎችና ለአመራር ስብሰባ ምክንያት በማድረግ በአበል መልክ” እየተከፋፈለ ነው። ወረርሽኝ ወደተከሰተበት አካባቢ በጊዜው ለመሄድ የተመደበው ገንዘብ ለሌላ ዓላማ በመዋሉ፣ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ሥራ አስቸጋሪ ሆኗል በሚል አብራርተዋል።

“በጤናው ዘርፍ መረጃ በየጊዜው ሪፖርት የሚደረግ ቢሆንም መንግሥት አስፈላጊውን የጤና ግብዓት እያቀረበ ወረርሽኙ ለምን ተከሰተ የሚል ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል በወረርሽኝ የተጠቁ ሕብረተሰብ ክፍሎች በሽታና ሞት በበላይ አካላት እንዲሰወሩ ተደርጓል” ስትል ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገች የጤና ባለሙያ ገልጻለች።

የጤና ዘርፍ አመራሮች “የወረርሽኝ መረጃ ይፋ ከሆነ የአካባቢው ገፅታ ያበላሻል” በሚል ወደ ክልል ሆነ ወደ ፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሪፖርት ባለማድረጋቸው የሰው ሕይወት እንዲያልፍ እያደረገ ነው።

የሕክምና ባለሙያዎች በጤና ተቋማት ያለውን ችግር ማውራት፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያ መጠየቅ ወይም የአገልግሎት ክፍተትን ማጋለጥ ከሥራ የሚያስባርርና የተለያዩ ጫናዎችን የሚያስከትል መሆኑን ገልጸዋል።

በአብዛኞቹ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የትርፍ ጊዜ ክፍያ ለረጅም ጊዜ ስላልተከፈላቸው፣ የጤና ባለሙያዎች በሥራ ገበታቸው ላይ ስለማይገኙ ሕብረተሰቡ የሚያስተናግድ አጥቷል።

ሕብረተሰቡ ወደ ግል ጤና ጣቢያዎች በውድ ዋጋ ለመታከም ሲሄድ፣ “አብዛኞቹ የተሳሳተ መድኃኒት በእርካሽ እንሸጣለን በሚሉ ተታልለው ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ” ብሏል።

በአሁኑ ወቅት የሕብረተሰቡን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው በሽታ “እውነትም የወባ ወረርሽኝ ስለመሆኑ በገለልተኛ የዓለም ጤና ተቋም ወይንም በሲዲሲ ምርመራ ተደርጎ መረጋገጥ መቻል አለበት” የሚል ጥያቄ ቀርቧል።

ነዋሪዎች “ሕብረተሰቡ እያለቀ ነው ድምጻችን አሰሙልን” በሚል ተማጽነው፣ የሚመለከታቸው አካላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሚዲያዎች “አስቸኳይ ምላሽ” እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድ ነዋሪ በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት የቤተሰቡን አባል ሦስት ጊዜ ወደ ጤና ተቋም መውሰዱን ገልጾ፣ በአካባቢው ባሉ ጤና ጣቢያዎች በቂ የሕክምና አቅርቦት ባለመኖሩ ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ መገደዱን አስረድቷል።

በዎላይታ ዞን እየተከሰተ ያለው አስደንጋጭ የወባ ወረርሽኝ በቀላሉ ሊቆጣጠርና ሊከላከል እየተቻለ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ያለው፣ በክልሉ እና በዞኑ ባሉ የጤና አመራሮች በሙስናና ብልሹ አሠራር ምክንያት ገንዘብ ለሌላ ዓላማ በመዋሉ እና መረጃ በመደበቁ እንደሆነ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን WT Media በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ባይሳካም፣ ምላሽ ሲያገኝ እንደሚያቀርብ ከወዲሁ እናሳውቃለን።

ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።

ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media