የመንግሥት መመሪያ አልተተገበረም፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ሲዘገይ፣ ሠራተኞች ‘ተጠያቂ አመራር ይፈለጋል’ አሉ!
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ በዚህ ወር እንደማይፈጸም የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) ከክፍያ ጋር ቅርበት ካላቸው አካላት አረጋግጧል።
ይህ መዘግየት የክልሉን አመራር ለከፍተኛ ትችትና ለተጠያቂነት ጥያቄ አጋልጦታልም ተብሏል።
WT Media ያነጋገራቸው ምንጮች፣ የአዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ከጥቅምት ወር ደመወዝ ጋር እንደማይፈጸም አረጋግጠዋል።

ሠራተኞች መጀመሪያ ላይ የቀድሞውን ነባር ደመወዝ ብቻ የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ጭማሪው ወደ ኅዳር ወር መተላለፉ ተሰምቷል።
የፌዴራል መንግሥት የደመወዝ ስኬል ማሻሻያውን ከመስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲተገበር መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል።
ይሁንና፣ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባሉ አካባቢዎች “በአፈጻጸም ችግርና በጉዳዩ ትኩረት አለመሰጠቱ” መዘግየቱ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ይላሉ የመረጃ ምንጮች።
የደመወዙ መዘግየት ለፋይናንስ አመራሮች የግል ጥቅም ማግኛ መንገድ እየሆነ ነው የሚል ከባድ ስጋት ተፈጥሯል።
“ገንዘቡ በባንክ በተቀመጠ ቁጥር ትርፉ የፋይናንስ ዘርፉን የሚመሩ ተሿሚዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ” የቅርብ ክትትል የሚያደርጉ አካላት ተናግረዋል።
የመንግሥትን አቅጣጫ የማይተገብሩና በደመወዝ የሚተዳደሩ ሠራተኞችን ችግር በጋራ የማይረዱ አመራሮች “ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባሉ” የሚል ጠንካራ ጥያቄ ቀርቧል።
አዲሱን ደመወዝ መክፈል ይቅርና፣ የደመወዝ ጭማሪውን የሚያረጋግጥ የጭማሪ ደብዳቤ እንኳን በብዙ መዋቅሮች አለመሰጠቱ መረጋገጡ፣ በጉዳዩ ላይ ያለው የአመራሮች ግድየለሽነት ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል ብሏል።

ምንጮች በጉዳዩ ላይ ያለው የአፈጻጸም መጓተት በቀጥታ የሠራተኞችን ኑሮ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት አስቸኳይ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚታየው ይህ የአፈጻጸም ችግር በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደሩ ሠራተኞችን የኑሮ ውድነት ችግር ይበልጥ የሚያባብስ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ችግሩ እንዲስተካከል መደረግ አለበት የሚል አጽንኦት ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media