ሰበር ዜና: በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መራዘምን የዘገቡ ባለሙያዎች መታሰራቸው ተገልጿል።
በክልሉ አሪ ዞን አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ መራዘሙን ዘግበው ያሰራጩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
WT Media ከስፍራው ባገኘውና ከዓይን እማኞች ጭምር ባረጋገጠው መረጃ መሠረት፦ የደመወዝ መዘግየት ዘገባ የአሪ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ባለሙያዎች የዞኑን የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ማናኩል ሳሎን አነጋግረው ነበር።
በዞኑ የአዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ መራዘሙን ተከትሎ ዘገባ አዘጋጅተው በዞኑ ኮሙኒኬሽን ፌስቡክ ገጽ ላይ በዛሬው ዕለት ጥዋት አሰራጭተው እንደነበር WT Media ተመልክቷል።

ዘገባውን ያሰራጩት ባለሙያዎች “ከክልሉ በተሰጠ ቀጭን ትዕዛዝ” ወደ ፖሊስ ጣቢያ በፓትሮል መኪና ተወስደው ታስረዋል የሚል መረጃ ከስፍራው አሁን ደርሶናል።
ይህ የፖሊስ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ፣ የደመወዝ መራዘሙን አስመልክቶ በዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ማኅበራዊ ትስስር ገጽ (ፌስቡክ) ላይ የወጣው ዘገባ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አረጋግጧል።
ይህ የአሪ ዞን ባለሙያዎች መታሰር የመጣው፣ WT Media ትናንት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ፣ “በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ በዚህ ወር እንደማይፈጸም” አረጋግጦ መዘገቡን ተከትሎ ነው።

ይህ ድርጊት የመንግሥት አካላት እውነታን ለመደበቅ እና የሠራተኛውን ሕገ መንግሥታዊ የመረጃ የማግኘት መብት ለመገደብ እየሠሩ መሆናቸውን የሚያሳይ አደገኛ ምልክት እንደሆነ በርካቶች እየገለፁ ይገኛል።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media