GridArt_20251110_153303630

ከስድስት ዓመት በፊት የመንገድ ስራ ያጠናቀቀው የቻይናው ተቋራጭ ድርጅት በህገወጥ አካሄድ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን እያመረተ በሚሸጠው ምርት ምክንያት በርካታ ማህበራት ከገቢያ እየወጡ እንደሆነ ተነግሯል።

የቻይናው ሁና ሀንዳ የተባለው የመንገድ ስራ ተቋራጭ ድርጅት በዎላይታ ዞን ለአስፋልት መንገድ ግንባታ እንዲውል የተፈቀደውን የጠጠር ማምረቻ ፈቃድ ከስድስት አመት በፊት ያጠናቀቀ ቢሆንም እስካሁን በህገወጥ መንገድ ጠጠር እያመረተ እንደሚሸጥና መንግስት ማግኘት ያለበት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በግለሰቦች እጅ እየገባ እንደሆነ WT Media ባደረገው ምርመራ ዘገባ ለማረጋገጥ ችሏል።

ሁና ሀንዳ የመንገድ ተቋራጭ ድርጅት የተባለ ባለቤትነቱ የቻይና የሆነ በዎላይታ ዞን ክንዶ ኮይሻ በሌ ከተማ አቅራቢያ ከስድስት ዓመት በፊት ያጠናቀቀውን የዎላይታ ሶዶ ዳውሮ አስፋልት መንገድ ግንባታ ግብዓትነት የጠጠር ማምረቻ ተክሎ ከዚያው አከባቢ ምርት እያመረቱ ሲጠቀም እንደነበር ያገኘነው የሰነድ መረጃ ያመለክታል።

ነገር ግን ተቋራጩ በውሉ መሠረት የአስፋልት መንገድ ስራ በተጠናቀቀበት ወቅት የጠጠር ማምረቻ ማቆም ሲገባ ከተለያዩ አካላት ጋር በመመሳጠር የምርት ሂደት አጠናክሮ በመቀጠል ምርቱን ወደተለያዩ አካባቢዎች ህግን ባልተከተለ ሁኔታ በአንድ ድጋፍ ደብዳቤ ብቻ እየወሰደ በመሸጥ ላይ እንደሚገኝም WT Media አረጋግጧል።

ይሄ አካሄድ የአከባቢውን ሀብት በህገወጥ መንገድ ከመመዝበር ባሻገር በአከባቢው በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ የጠጠር ማምረት ፈቃድ አግኝተው የተለያዩ ማሺኖችን በመግዛት በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነም ከቅሬታ አቅራቢዎች ለሚዲያችን የደረሰው በሰነድ የተደገፈ መረጃና ማስረጃ ያስረዳል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚገልጹት ከዚህ በፊት በዎላይታ እና አከባቢው ላይ በዘርፉ ለመሰማራት ፈቃድ አውጥተው ወደ ተግባር የገቡ በዚህ የቻይናው ተቋራጭ አማካይነት ያለጨረታ በህገወጥ መንገድ ለተለያዩ ድርጅቶች ጠጠር እየቀረበ በመሆኑ ከተለያዩ ብድር ተቋማት የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ ባለመቻላቸው ከ90% በላይ የተደራጁ ማህበራት ተበትነው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ለአደጋ ማጋለጡን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በዚሁ በዘርፉ በማህበር ተደራጅተው የነበሩና በህጋዊ መንገድ ተወዳድረው ምርት ለማቅረብ ህጋዊ አሰራር ዝግ በመሆኑ በከፍተኛ ገንዘብ የገዙትን ማሽነሪዎችን ጭምር በቀላል ዋጋ ሽጠው ተስፋ በመቆረጥ ከስራው እየወጡ እንደሆነም ጠቁመዋል።

እነኚህ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ለሚመለከታቸው መንግሥት አካላት ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ቢጠየቁም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይሄው የቻይናው ሁና ሀንዳ የመንገድ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ከስድስት ዓመት በፊት ያጠናቀቀውን አስፋልት መንገድ ግንባታ ግብዓትነት የሚጠቅመውን በውሉ መሰረት አጠናቅቆ መውጣት ሲገባው ለምን በህገወጥ መንገድ ጠጠር ማምረትና በህገወጥ መንገድ መሸጥ አስፈለገ ወይንም እውነትም ተቋራጩ ስለጉዳዩ ያውቃል የሚለውን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም ካገኘን እንመለስበታለን።

በተጨማሪም WT Media የአከባቢው ተፈጥሮ ሀብት የሆነው በጥቂት ግለሰቦች መመሳጠር በየቀኑ በበርካታ ጭነት መኪኖች ህጋዊ አሰራርን ካለመከተል በተጨማሪ ለመንግሥት ተገቢ ግብር ሳይከፈልበት እየተዘረፈ ወደ ተለያዩ አከባቢዎች ለሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች እንዲሸጥ እየተደረገ ስለሚገኘው ጉዳይ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

ክፍል ሁለት ላይ የዚሁ ዝርዝር የምርምራ ዘገባ እናቀርባለን። ለህገወጥ ተግባር እየዋሉ የሚገኙ ሀሰተኛ ደረሰኞች፣ የድጋፍ ደብዳቤዎች እና ሌሎች ሰነዶችን ለሚመለከታቸው አካላት ስለሚደርሱና በህገወጥ መንገድ ሀብት እየመዘበሩ ይገኛሉ ተብሎ የተጠቀሱ አካላት ምላሽ እስኪሰጡበት ለጊዜው አላቀረብንም።