የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ዛሬ ይፈጸማል ወይ? WT Media በፋይናንስ ቢሮ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦታው ላይ ሆኖ ይከታተላል!
በመንግሥት ሠራተኞች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የመስከረም እና የጥቅምት ወራት የደመወዝ ጭማሪ ውዝፍ ክፍያ ዛሬ ኅዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሚፈጸም የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) የክፍያውን ሂደት በጥብቅ እየተከታተለ ይገኛል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተፈሪ አባተ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ክፍያው ዛሬ እንደሚፈጸም ቃል ገብተው ነበር።
አቶ ተፈሪ በክልሉ ሥር ከሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች መረጃዎች ተደራጅተው መምጣታቸውን አስታውሰው፣ የመስከረም እና የጥቅምት ወር አዲሱ ጭማሪ ደመወዝ እንዲከፈል ለባንክ መላኩን ገልጸው ነበር።

ክልሉ ሥር የሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ሪጅናል ፖሊስ፣ እንዲሁም ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ዛሬ ኅዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4:30 ድረስ ገንዘቡን ከባንክ ማግኘት የሚችሉ መሆናቸውን አቶ ተፈሪ በትናንትናው ዕለት ገልፀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ በሁሉም መዋቅር ደመወዝ ክፍያ እንደሚፈጸም ቃል የገባ በመሆኑ፣ WT Media የክፍያውን ሂደት በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል።
የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ዘጋቢዎችና ምንጮች በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች አካባቢ በቦታው ላይ ሆኖ የእንቅስቃሴውን ሂደት እየተከታተሉ ነው።
WT Media፣ የክልሉ መንግሥት የገባውን ቃል በተመለከተ መረጃ ያለን ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ትክክለኛውን ሂደት እንዲያደርስልን ጥሪ ያቀርባል።
ይህ ክፍያ የሚፈጸመው፣ WT Media ቀደም ባሉት ዘገባዎቹ በአፈጻጸም ችግር፣ ትኩረት በማጣትና በፋይናንስ አመራሮች የግል ጥቅም ስጋት ምክንያት ክፍያው መዘግየቱንና ለኅዳር ወር መተላለፉን ሲዘግብ ከቆየ በኋላ ነው። በዛሬው ዕለት የገቡት ቃል ተግባራዊ መሆን አለመሆኑ የብዙ ሠራተኞችን ትኩረት ስቧል።