“ሰላምን” አፍኖ ‘የሰላም አምባሳደር’ መሸለም አሳፋሪ ነው! “ጥብቅ የሌብነት ወዳጅነትን” ለማፅናት የማንነት ጥያቄዎችን በኃይል ለሚያፍነው የተሰጠው ሽልማት የሰላም ትርጉም የሳተና ለተበደሉት ንቀት ማሳየት ነው” – የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ውስጥ የዘይሴ ሕዝብ የልዩ ወረዳና ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ በግድያና በእስራት መታፈኑ አሳሳቢ የሀገር ስጋት እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እጩ ዶክተር ዎና ወንድፍራው ገልጸዋል።
WT Media እጩ ዶ/ር ዎናን ባነጋገረበት ቆይታ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ይህንን ሕዝባዊ ጥያቄ በማፈን ለዘር ማጥፋት ዘመቻ መዳረጋቸውን እየተዘገበ ባለበት ወቅት፣ “የሰላም አምባሳደር” ተብለው መሸለማቸው የመንግሥትን “የወደቀ ስብዕና” የሚያሳይ ድርጊት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

እጩ ዶ/ር ዎና፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “ትንሿ ኢትዮጵያ” እንደሆነች ገልጸው፣ ይህቺ ከፍተኛ ሀብትና ብዙ ማንነት ያላት ክልል ችግሮችን በጊዜ ከመፍታት ይልቅ ማፈንንና መግደልን በመምረጡ አጠቃላይ ለሀገሪቱ ስጋት እየሆነ መጥቷል።
“የሰሜኑ የወልቃይት ጠገዴ የአሁኑ የጦርነት ዋና ማዕከል ሆነው ሀገር ለማፍረስ የደረሰው በእንጭጩ ምላሽ ያለመስጠት ችግር የፈጠረው እንደሆነ ሁሉም መረዳት ይችላል” ሲሉ፣ የዘይሴን ጥያቄ ማፈን ለቀጣይ ተመሳሳይ አደጋ መጋበዝ እንደሆነም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁርና ተመራማሪ እጩ ዶ/ር ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( #WTMedia ) አስረድተዋል።
በክልሉ የሚነሱ “እኔ ዘይሴ ነኝ፣ ቁጫ ነኝ፣ ዶርዜ ነኝ” የሚሉ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን “እናንተ ማንነት የላችሁም፣ እናንተ ጋሞ ናችሁ” በሚል በግድ በመጫን እየተፈጸመ ያለው ግድያና ንብረት ማውደም፣ “አንድ ሰው ስሙ አበበ ሆኖ ሳለ አይ አንተ ከበደ ነህ ብሎ እንደማስገደድ ነው” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
ምሁሩ እንደሚሉት፣ መንግሥት በቸልተኝነት ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት “ዜጎቿ ጦረኛ፣ ተፋላሚና አማፂያን ሆነው የሚቀሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል”። ሕዝቡ “ከመንግሥት ጋር መዋጋት ይችላል” የሚል አስተሳሰብ በውስጡ ያድጋልና ይህም ለቀጣይ ትውልድ ስጋት ነው።
በአሁኑ ሰዓት የአርባምንጭ- ኮንሶ-ቡርጂ- አማሮ መንገድ ዝግ ነው። ይህ ችግር ምላሽ ካላገኘ፣ ቀጣይ ወደ ዎላይታ እና ጂንካ የሚመጣው መንገድ የሚዘጋ ኃይል ሆኖ ከመደራጀቱ በፊት ለዘይሴ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት “ማትረፍ እንጂ ኪሳራ የለውም” የሚል ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል።
“በተለይ ለአቶ ጥላሁን ከበደ የሰላም አምባሳደር ነው ብሎ መሸለም አሳፋሪና የመንግሥትን የወደቀ ስብዕና ባለቤት መሆኑን ያሳያል” ያሉት እጩ ዶ/ር ዎና፣ አቶ ጥላሁን በወንጀሎቻቸው ተሰልተው ወኅኒ መውረድ ሲገባው የሰላም አምባሳደር ተብሎ መሸለሙ “ሃይማኖትም ተቋምም እንደሌለ” ያሳያል ብለዋል።
ምሁሩ፣ በፌዴራል ደረጃ በብልጽግና ውስጥ የተሸሸጉ እንደ አቶ አገኘው ተሻገር ያሉ የውሸት ኃይሎች ከአቶ ጥላሁን ከበደ ጋር ባላቸው “ጥብቅ የውንብድና የሌብነት ወዳጅነት” ምክንያት የማንነት ጥያቄዎች በኃይል እንዲታፈኑና ክልሉን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“የፌዴራል መንግሥትም የክልሉን አመራሮች የውሸት ሪፖርት ከመቀበል ይልቅ ወርዶ አይቶ ለሕዝቡ ምላሽ መስጠት አለበት” የሚል አጽንኦት ሰጥተዋል።
የማንነት ጥያቄ ቀላል ጥያቄ ሳይሆን ሕዝቡ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከፍሎ ለሀገር ስጋት ሊሆን ስለሚችል፣ ዘግይቶ ምላሽ መስጠት ዋጋ ያስከፍላል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ማሳሰቢያ፦ #WTMedia በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media